ኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ያላትን እምቅ አቅም በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በትኩረት ይሰራል-መላኩ አለበል

159

(ኢዜአ) ጥቅምት 25/2015  ኢትዮጵያ በ8ኛው 'የአፍሪካ ሶርሲንግ ፋሽን ሳምንት' የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ እምቅ አቅሟን በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በትኩረት እንደሚሰራ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።

8ኛው 'የአፍሪካ ሶርሲንግ' ዓለም አቀፍ የጨርቃ ጨርቅና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶች የንግድ ትርኢትና የኤግዚቢሽን ሳምንት በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ዛሬ ተከፍቷል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የአምራች ዘርፉን በተለይም የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪውን ለማጠናከርና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በስፋት እየተሰራ ነው።

የፋሽን ትርኢት ሳምንቱ ኢትዮጵያን የበለጠ ለማስተዋወቅና ኢንቨስትመንት ለመሳብ ተጨማሪ አቅምና ጉልበት ይሆናል።

አምራች ኢንዱስትሪው በኮቪድ 19፣ ከአጎዋ መሰረዝና  ሌሎች  የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ችግሮች በተፈጠረው ችግር ጫና ተፈጥሮበት የነበረውን አምራች ኢንዱስትሪ ለማነቃቃት ያግዛል ነው ያሉት።

በሀገሪቱ የተጀመረው የሰላም ሂደትም ለኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ  ሌላው ትልቅ ተስፋ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት በጨርቃ ጨርቅና የልብስ ጥበብ ሙያ ትታወቃለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ  የጥጥ ምርቶችን ለተለያየ የባህል አልባሳት የመጠቀም የረጅም ዓመታት ያዳበረችውን የሽመና ሙያ ለማሳደግ  እየሰራች መሆኗን እንዲሁ።

የፋሽን ትርኢት ሳምንቱ ለዚህ ጥሩ ልምድ እንደሚገኝበት ጠቅሰው፤ አምራቾች የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት፣ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትና ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንደሆነ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አዎር ጀርመን የአፍሪካን አምራች ዘርፍ እየደገፈች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የኢትጵያን አምራች ዘርፍ በመደገፍ በኩል ረጅም ዓመታት ታሪክ እንዳስቆጠረ ጠቅሰው፤ ድጋፉና ትብብሩ በዋናነት የቴክኖሎጂ ሽግግርና የማማከር አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይ ዳይሬክተር አውሪሊያ ፓትሪዚያ የፋሽን ሳምንቱ ልምድ ለመለዋጠጥና የአፍሪካን ኢንዱስትሪ አቅም ለማጎልበት የሚያበረክተው አስታዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በጀመረችው 'ኢትዮጵያ ታምርት' ንቅናቄ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ  ነው የጠቆሙት።

በዚህ የንግድ ትርኢትና ኤግዚቢሽን ከ30 ሀገራት የተውጣጡ 200 አምራቾች ተሳታፊ ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ 39ኙ የኢትዮጵያ አምራቾች ናቸው።

በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በዛሬው ዕለት የተከፈተው የንግድ ትርኢትና ኢግዚብሽን ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀናት የሚቆይ ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም