የሰላም ስምምነቱ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ያሳየ ነው-ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሰላም ስምምነቱ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ያሳየ ነው-ነዋሪዎች

አርባ ምንጭ (ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2015 በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ለዓለም ያሳየ ነው ሲሉ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ጩባ ጭኖ ለኢዜአ እንደገለጹት በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የነበረው የሰላም ንግግር በኢትዮጵያ አሸናፊነት በመጠናቀቁ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
"በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል የተደረገው የሰላም ውይይት በአፍሪካ ህብረት መሪነት ተካሂዶ መጠናቀቁና ፍጻሜ ማግኘቱ አፍርካውያን የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት የሚያስችል አቅም እያዳበርን መምጣታችን ያስመሰከረ ነው" ብለዋል።
ውይይቱ በሁለቱም ስምምነት መጠናቀቁ አገሪቱ ለሰነቀችው ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመላክተዋል።
መንግስት ለሰላም ሲል በሀይማኖት መሪዎች፣ በእናቶችና በሌላም አማራጭ የሄደባቸው ርቀቶች ተገቢና የህዝቡን ጥቅም ያስቀደመ እንደነበር አስታውሰዋል።
ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት ሁሉም አካል ሊተጋ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ለሀገሪቱ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት አስፈላጊውን በማድረግ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።
"መንግስት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማይጎዳና በማያስነካ መልኩ አስቀድሞ ያቀረባቸው ሀሳቦች በሰላም ስምምነቱ ተቀባይነት ማግኘታቸው በሀገር ህልውና ጉዳይ ላይ ያለውን ጥንቃቄ የሚያሳይ በመሆኑ ኮርተናል" ያሉት ደግሞ አቶ አይናለም ኡንዳ ናቸው ።
"ውይይቱ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሚያስችል መልኩ መቋጫ ማግኘቱ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ያሉንን ሀብቶች በሙሉ በመጠቀም ከድህነት ለመላቀቅ እየተደረገ ያለውን ትግል በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለማሳካት የሚያግዝ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።
አቶ ይገዙ በየነ የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው "በአፍሪካ ህብረት መሪነት የተከናወነው የሰላም ንግግር ላልተገባ ጣልቃ ገብነት ዕድል የማይሰጥና በር የዘጋ ነው" ብለዋል።