ኢትዮ ቴሌኮም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ነው

128

ጋምቤላ  (ኢዜአ)   ጥቅምት 25/2015 ኢትዮ ቴሌኮም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

ተቋሙ በጋምቤላ ክልል በአቦል 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዘረጋውን የዲጅታል የቤተ መጸህፍት አገልግሎት ዛሬ አስመርቆ ለተጠቃሚዎች አስረክቧል።

በኢትዮ ቴሌኮም የምዕራብ ሪጅን የጋምቤላ ጽህፈት ቤት የኦፕሬሽናል ዳይሬክተር አቶ አወል አብዳላ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ተቋሙ የቴሌኮም አገልግሎቱን ተደራሽ ከማድረግ  ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ ነው።

ተቋሙ በተለይም የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ በመላ ሀገሪቱ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት በጋምቤላ ክልል በዕለቱ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃውን ጨምሮ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ሁለት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ዲጅታል የቤተ መጸህፍት አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለ1ሺህ 500 ተማሪዎች ሙሉ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመው በቀጣይም ሌሎች ትምህርት ቤቶች የዲጂታል ቤተ መጸህፍት አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል ዳይሬክተሩ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የማህበራዊ አማካሪ አቶ ፒተር አማን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም በክልሉ የቴሌኮሙን አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ ጎን ለጎን የትምህርቱን ዘርፍ በማገዝ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እያደረገ ላለው ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።

በትምህርት ቤቶቹ የተዘረጋው ዘመናዊ ቤተ መጸሐፍት አገልግሎት ተማሪዎች ዘመኑ የደረሰበትን የኢንፎርሜሽን አገልግሎት በመጠቀም እራሳቸውን ለማብቃት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

ተቋሙ በትምህርት ቤቱ የዘረጋው ዲጂታል ቤተ መጸህፍት አገልግሎት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ መሳካት ዓይነተኛ ፍይዳ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ  ምክትል ኃላፊ አቶ ኮንግ ጆክ ናቸው።

በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮም የትምህርት ልማት ስራውን ለማገዝ እያደረገ ላለው ጥረት ቢሮው ምስጋና ያቀርባል ብለዋል።

በዕለቱ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ዲጂታል ቤቱ መጸህፍቱ 21 ዴስክ ቶፕ ኮምፒተሮችና የ11 ሜጋ ባይት ነፃ ኢንተርኔት አገልግሎት ያለው ነው።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም