ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሠላም ስምምነቱ መደሰታቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሠላም ስምምነቱ መደሰታቸውን ገለጹ
(ኢዜአ) ጥቅምት 25 ቀን 2015 በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት በፌዴራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ በተደረሰው የሠላም ስምምነት መደሰታቸውን ገለጹ።
የቱርኩ ዜና ወኪል አናዶሉ ‘South Africa’s Ethiopian diaspora welcomes agreement for peace’ በሚል ርዕስ በሰራው ዘገባ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በስምምነቱ ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት ጠይቋል።
ጆሃንስበርግ ከተማ ውስጥ በንግድ ሥራ የተሰማራው ሱሌማን ሁሴን “በሠላም ድርድሩ ውጤት በጣም ደስተኛ ነኝ፤ ይህ የሠላም ስምምነት ለኢትዮጵያ ዕድገትና መረጋጋት መሰረት እንደሚጥል እምነት አለኝ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
የሠላም ስምምነቱ እውን እንዲሆን የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች እና የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በማመስገን።
በተመሳሳይ በንግድ ሥራ የተሰማራው ሙዚያህ ንቱሉ በበኩሉ በፕሪቶሪያ የተደረገው የሰላም ድርድር ውጤት ለኢትዮጵያ የተሻለ ነገር አስገኝቷል ብሏል።
ወጣት ዮናስ በበኩሉ ከፕሪቶሪያ የተሰማው ዜና አስደሳች እንደሆነ ነው የገለጸው።
“ይህ በጣም ደስ የሚል ዜና ነው። እኛ አንድ ህዝብ ነን፤ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን፤ በማለትም የሠላም ስመምነቱን አወድሷል።
ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ኤልዛቤት ደመወዝ በሰጠችው አስተያየት በተደረሰው የሠላም ስምምነት መደሰቷን ገልፃ ደቡብ አፍሪካ ላደረገችው መስተንግዶ አመስግናለች።
የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ህብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ የሰላም ስምምነቱ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካ ቀንድ ብሎም ለመላው አፍሪካ ‘አዲስ ንጋት’ ሲሉ መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያውያን የዲያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።