የከሰም ግድብ የውሃ ማስተንፈሻ በር አገልግሎት ባለመስጠቱ ግድቡ ሞልቶ ስጋት ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የከሰም ግድብ የውሃ ማስተንፈሻ በር አገልግሎት ባለመስጠቱ ግድቡ ሞልቶ ስጋት ፈጥሯል
አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 በኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ የተገነባው የከሰም ግድብ የውሃ ማስተንፈሻና መቆጣጠሪያ በር አገልግሎት ባለመስጠቱ ግድቡ ሞልቶ ይፈሳል በሚል በአሚባራ ወረዳና አካበባቢው ስጋት ፈጥሯል። ግድቡን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን በበኩሉ አሁን ላይ የግድቡ የውሃ ሙላት በተወሰነ መጠን እየቀነሱ በመሆኑ ስጋቱ ቀንሷል፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ስራዎች ተጀምሯል ብሏል። ለከሰም ስኳር ፋብሪካ ግብዓት የሚውል ሸንኮራ አገዳና ለአፋር ቆላማ አካባቢዎች ለመስኖ ልማት ተብሎ በአፋር፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ በከሰም ወንዝ ላይ የተገነባው ከሰም ግድብ አሁን ላይ 500 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ መጠን ይዟል። በኢትዮጵያ ውሃ ስራዎች ድርጅት የሲቪል ስራው የተከናወነው ግድቡ፣ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ክፍሉ ደግሞ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሸን/ሜቴክ/ ነበር ተገንብቶ ከሶስት ዓመታት በፊት ወደስራ የገባው። አቶ አህመድ መሐመድ በተወለዱበት አፋር ክልል አሚባራ ወረዳ ከ15 ዓመት በፊት ከነበራቸው የአምስት ሄክታር መሬት ተነስተው፤ የእርሻ ልማታቸውን በማስፋፋት አሁን ላይ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሄክታር መሬት ላይ በተለያዩ የበረሃ ሰብሎችን ያለማሉ። በ2007ዓ.ም የአዋሽ ወንዝ ፈሶ የደረሰ የጥጥ ማሳቸውን እንዳወደመባቸው የሚገልጹት አቶ አህመድ፤ አዋሽ በተለይም የእርሻ ልማታቸው በሚገኝበት በአሚባራና መልካ ወረር ወረዳዎች ዛሬም የስጋታቸው ምንጭ ሆኖ ቀጥሏል። ከወንዙ ባሻገር በአካባቢው የሚገኘው የከሰም ግድብ መሙላቱን ተከትሎ የግድቡ ውሃ ፈሶ ወደ አዋሽ ወንዝ በመቀላቀል በሰብል ላይም ሆነ በአካበባዊው ነዋሪዎች ላይ ከባድ አደጋ እንዳያደርስ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ያነሳሉ። በአሚባራ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ከፍተኛ ባለሙያና የወረዳ አስተዳደሩን በመወከል የስጋት አስተያየታቸውን ለኢዜአ ያገሩት አቶ አሰፋ አየለ የከሰም ግድብ ለልማት ያለው ፋይዳ የጎላ ቢሆንም ከመጠን በላይ ውሃ መያዙ ማህበረሰቡ ለችግር ያጋልጠናል የሚል ስጋት መፍጠሩን ተናግረዋል። የሚመለከታቸው አካላት የግድቡን ውሃ እንዲያስተነፍሱ ላቀረብነው ጥያቄ የግድቡ ማስተንፈሻ በር መበላሸቱን ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸው፤ የፌዴራል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲያበጅለትም ጠይቀዋል። የኢዜአ ዘጋቢ ጉዳዩን በስፍራው ተገኝቶ እንደተመለከትውም የከሰም ግድብ በዘንድሮው የክረምት ዝናብ የውሃ መጠኑ መጨመሩን አረጋግጧል። በስፍራው ያገኘነው የግድቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱሮ ዳልዮ ግድቡ በዘንድሮው የክረምት ወቅት በአማካይ ከ20 እስከ 40 ሴንቲ ሜትር በየቀኑ ሲጨምር እንደነበር ገልጸው፣ በዚህ ፍጥነት ውሃው ሞልቶ ይፈሳል የሚል ስጋት እንደነበራቸው ተናግረዋል። ሞልቶ ለመፍሰስ 11 ሴንቲ ሜትር ሲቀረው ግን አሁን ላይ የውሃ መጠኑ እየቀነሰ መሆኑን ገለጸው፤ ስጋቱም ቀንሷል ብለዋል። ጎርፍ ይፈጥራል ተብሎ የተሰጋውም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተሰራው የማስተንፈሻ በር/ጌት/ ከተገነባ ጀምሮ አገልግሎት ባለመስጠቱ ነው ብለዋል። ሜቴክ የውሃ መቆጣጠሪያ በሩን እንዲያስተካከል በተደጋጋሚ ቢጠየቀም ምላሽ ሊሰጥ እንዳልቻለ ነው የተናገሩት። በኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የግድብና መስኖ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ላቃቸው ግድቡ ያለበት ችግር መኖሩን አምነው፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ድርጅት የከሰም ግድብ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ግድቡ ያለበት ሁኔታ የጠየቅነው የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳመነ ዳሮታ ከሰም ግድብ ፕሮጀክት ቀደም ሲል ውሃ የመያዝና ሌሎች ችግሮች እንደነበረበት ገልጸው፤ አሁን ላይ ደግሞ ውሃ መያዙ የሚያስደስት እንደሆነ ገልጸዋል። ነገር ግን ግድቡ ስጋት ውሰጥ እንዲገባ ምክንያት የሆነው የግድቡን ውሃ በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል የማስተንፈሻ አገልግሎት ያለመስጠት ችግር ከተፈታ ግድቡ ከጎርፍ ስጋት ተላቆ ወደ ሙሉ ልማት የሚለወጥ ነው ብለዋል።