የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚያጸና በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለተግባራዊነቱ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

21

ጥቅምት 25/2015 /ኢዜአ/ የሰላም ስምምነቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነት የሚያጸና በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬደዋን ሁሴን ተናገሩ፡፡

የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴ አባላት የስምምነቱን አጠቃላይ ሂደትና የቀጣይ ስራዎችን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት ለሁለቱ ምክር ቤቶች አፈጉባኤዎች፣ ለክልል ርእሳነ መስተዳድሮች፣ ለከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ለብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡

May be an image of 7 people, people standing and indoor

የኮሚቴው አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እንዳሉት፤ ስምምነቱ በዋናነት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም፣ ሉዓላዊነትና የግዛት እንድነትን ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ስምምነቱ  የኢትዮጵያ ህዝቦችን የጋራ ጥቅም ባስከበረ መልኩ መጠናቀቁን ነው የተናገሩት፡፡

በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ ሁለት የታጠቀ ሀይል ሊኖር እንደማይችልና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ማክበር እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አኳያ ከህገ መንግስት ውጪ ያሉ እንቅስቃሴዎች ቆመው በትግራይ ክልል  በህገ መንግስቱ መሰረት ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ  ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋምም ተናግረዋል፡፡

ያለን አማራጭ እና መፍትሄ በጋራ ተሳስሮ መሄድ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ ከዚህ አኳያ ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ቀደመው ማህበራዊ ትስስር እንዲመለሱ በጋራ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

May be an image of 8 people, people standing, suit and indoor

የደረሰው ጉዳት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የወደሙ ተቋማትን ጨምሮ የመልሶ ግንባታ ስራዎች በጋራ ርብርብ  ሊከናወኑ ይገባል ብለዋል፡፡

የትስስርና የተግባቦት ስራዎችም የህዝቦችን መጻኢ የጋራ ጉዞ ታሳቢ ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

ያሉንን አቅሞች በማስተባበር ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

በግጭቱ ምክንያት በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እንዲሁም በሌሎች መስኮች የደረሰውን ጫና በማስተካከል ረገድም በትብብር መስራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ በተለይ የመገናኛ ብዙሃን ቁርሾዎችን ማባባስ ሳይሆን ዜጎች ከችግሩ ተምረው በቀጣይ አብሮነታቸውን አጠናክረው የሚሄዱበትን ሁኔታ መፍጠር ላይ ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በግጭቱ የተጎዳችው የሁላችንም የጋራአገር የሆነችው ኢትዮጵያ ናት ያሉት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ በመሆኑም ስምምነቱ በሁሉም ዜጎች ተሳትፎ  ኢትዮጵያን ከፍ ለማድረግ እድል እንደሚፈጥር አንስተዋል፡፡

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሰላም ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሰሩ ኣካላትን ደግሞ በጋራ ማስቆም እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ሁሉም ዜጋ ለስምምነቱ ተግባራዊነት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መድረኩ የቀጣይ ስራዎች ትብብር ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም