ቀጥታ፡

ስምንተኛው የአፍሪካ ሶርሲንግና ፋሽን ሳምንት ተጀመረ

ጥቅምት 25 /2015(ኢዜአ) በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በአልባሳት፣ በጥጥ ምርት፣ በቴክኖሎጂና በቤት ማስዋብ ኢንዱስትሪዎች ላይ በማተኮር የሚካሄደው ስምንተኛው የአፍሪካ ሶርሲንግ ኤንድ ፋሽን ሳምንት ዛሬ በስካይላይት ሆቴል ተጀምሯል።


በመርሐግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ናሲሴ ጫሊ፣ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር ፣የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) የኢትዮጵያ ተወካይና ቀጣናዊ ዳይሬክተር አውሬሊያ ፓርቲዚያ ካላብሮ ተገኝተዋል ።


በአፍሪካ ሶርሲንግ እና የፋሽን ሳምንት ላይ ከ30 ሀገራት የተውጣጡ 200 አምራቾች ይሳተፋሉ ተብሏል።

በንግድና ትርኢቱ ተሳታፊዎች መካከል 39 የሚሆኑት የኢትዮጵያ አምራቾች መሆናቸው ተነግሯል።


መርሐ-ግብሩ አምራቾች የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት፣ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትና ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንዲሁም የጨርቃጨርቅ አምራቾችን ለማጠናከርና አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የንግድ ድርሻና ደረጃ ለማሳደግ የሚያግዝ እንደሆነ ተገልጿል።


ለአራት ቀናት በሚቆየው መርሐግብር የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና መሴ ፍራንክፈርት በትብብር ያዘጋጁት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም