ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ሀገራችን በገጠማት ፈተና ሳይበገሩ ህዝቡን ለአንድነት፣ ለሀገር ሉዐላዊነትና ለልማት በማነሳሳት አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል-ነዋሪዎች

16

አርባ ምንጭ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ)  ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ከለውጡ ማግስት  ጀምሮ ሀገራችን በገጠማት ፈተና ሳይበገሩ ህዝቡን ለአንድነት፣ ለሀገር ሉዐላዊነትና ለልማት በማነሳሳት አመርቂ ውጤት አስመዝግበዋል ሲሉ የአርባ ምንጭ ነዋሪዎች ተናገሩ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አርባ ምንጭ እና አካባቢውን መጎብኘታቸው አንድነታቸውን በማጠናከር በልማት ውጥኖች ላይ እንዲተጉ መነሳሳት እንደፈጠረላቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋሞ እና ጎፋ ዞኖች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ጎብኝተው ከህብረተሰቡ ጋር ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስራ ጉብኝት አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ጉብኝቱ ማህበረሰቡ ለልማት ይበልጥ እንዲነሳሳ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የጋሞ እና የጎፋ ዞኖች ህዝብ አገራዊ ለውጡን በመደገፍ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን በማበርከት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ለሁሉም ዜጎች ትኩረት ሰጥተው በየአካባቢው ያለውን የልማት እንቅስቃሴ በመጎብኘት ማበረታታቸው የበለጠ ውጤት ለማምጣት እንደሚያስችልም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

መንግሥት ያቀዳችው የልማትና የብልጽግና ትልሞች እንዲሳኩ በተዋረድ የሚገኙ አመራሮች ከህዝቡ ጋር በቅርበት መስራት እንዳለባቸው ትምህርት የሰጠ ጉብኝት እንደሆነም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝቡ ያሳዩት ፍቅርና ክብር አስደሳች መሆኑን ገልጸዋል።

የጋሞ ዞን በቱሪስት መስህቦች፣ በፍራፍሬ፣  በዓሣ፣ በእንስሳትና  በሸማ ጥበብ  ያለውን  ሀብት  በማልማት መበልጸግ የሚችል የታደለ አካባቢ መሆኑን አመላክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲፋጠን በአካባቢያችን የሚገኙ የተፈጥሮ ጸጋዎችንና ሀብቶችን በማልማት ጥቅም ላይ እንድናውል ይበልጥ አነሳስቶናል ብለዋል።

ዞኖቹ ያላቸውን  ሀብቶች  ጥቅም ላይ  ለማዋል  የእርስ በርስ  ትስስርን ማጠናከር ፣ በፍቅርና በትብብር በመስራት ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝትና ውይይት ወሳኝነት እንዳለው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም