3ኛው የኢትዮ-ዩናይትድ ኪንግደም የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም በለንደን ተካሄደ

163

ጥቅምት 24/ 2015 (ኢዜአ) ሶስተኛው የኢትዮ-ዩናይትድ ኪንግደም የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በለንደን ተካሄደ።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ኢትዮጵያ እያካሄደች በምትገኘው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለግሉ ዘርፍ ሰፊ የኢንቨስትመንት ምህዳርን እየፈጠረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

የወጪ ንግዱን በማሳደግ ወደ ተለያዩ አገራት የሚላኩ ምርቶችን በአይነትና በመጠን መጨመር በኢኮኖሚው ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑ ገልጸዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በበኩላቸው የአገሪቷ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ሊያፈሱባቸው የሚችሉበት ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

ግብርና፣የግብርና ማቀነባበሪያ፣መሰረተ ልማት፣ጤና፣ቱሪዝም፣ኃይል እንዲሁም አቪዬሽን ከአማራጮቹ መካከል እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

መንግስት እንደ ቴሌኮምዩኒኬሽኑ መስክ ፋይናንስን ለግሉ ዘርፍና ለውጭ ባለሀብቶች ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የዩናይትድ ኪንግደም ባለሃብቶች ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጭ ተጠቅመው በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ አምባሳደር ተፈሪ ጥሪ አቅርበዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ዙሪያ ገለጻ መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

በፎረሙ ላይ ከ100 የሚበልጡ የዩናይትድ ኪንግደም ባለሀብቶች የተሳታፉ ሲሆን የአንድ ለአንድ የንግድ ውይይቶች እንዲሁም የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትስስር መድረኮች መካሄዳቸውን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም