ለሰላም ስምምነቱ ስኬታማነት ቁርሾና ቂምን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ሰላምና ብልጽግና በጋራ መቆም አለብን-የመዲናዋ ሴቶች

17

ጥቅምት 24 ቀን 2015 /ኢዜአ/ ለሰላም ስምምነቱ ስኬታማነት ቁርሾና ቂምን ወደ ጎን በመተው ለሀገር ሰላምና ብልጽግና በጋራ መቆም አለብን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ሴቶች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል የተካሔደው የሰላም ስምምነት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱንና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ ትላንት መጠናቀቁ ይታወሳል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሴቶች በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ሲካሔድ የቆየው የኢፌዴሪ መንግስትና የህወሃት የሰላም ውይይት በስኬት በመጠናቀቁ መደስታቸውን ተናግረዋል።

የሰላም ዋጋ የማይተመን መሆኑን የተናገሩት ወይዘሮ ሩት ስንታየሁ፤ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለዋል።

ወይዘሮ አልማዝ አልዋሽ በበኩላቸው ወደ ሰላም መምጣት መቻሉ ትልቅ እርምጃ ነው ብለዋል።

በጦርነቱ ሳቢያ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶች የደረሱ ቢሆንም ከዚህ ትምህርት ወስዶ በቀጣይ ጠንካራ ሀገር መገንባት ላይ በጋራ መረባረብ ይገባል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሀረግ ብርቄ ናቸው።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰላምን በዘላቂነት ማስፈን የሚያስችሉ አበርክቶዎችን መፈጸም እንደሚጠበቅበትም ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

በተለይ ጦርነትንና ዘረኝነትን ከሚሰብኩ አስተሳሰቦች ራስን በማራቅ ለሀገር ሰላምና ብልጽግና የሚያረጋግጡ ስራዎች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

ለሰላም ስምምነቱ ስኬት የነበረውን ቁርሾና ቂም ወደ ጎን በመተው ለሀገር ሰላምና ብልጽግና በጋራ መቆም አለብን ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ ሀገሪቱ ከድህነት እንድትወጣ በጋራ ጠንክረን እንስራ ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም