ኢትዮጵያ የዘመኑን የ5-ጂ ኔትወርክ አገልግሎት መጠቀም ከጀመሩ ጥቂት የዓለም አገራት ተርታ ውስጥ ገብታለች- ፍሬህይወት ታምሩ

ጥቅምት 24 ቀን 2015 /ኢዜአ/  ኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበትን የመጨረሻው ደረጃ አምስተኛ ትውልድ የ5-ጂ ኔትወርክ አገልግሎትን ከሚጠቀሙ ጥቂት ሀገራት ተርታ መካተቷን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ኩባንያው በአዳማ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአሁኑ ወቅት የመጨረሻ ደረጃ የሆነውን የአምስተኛ ትውልድ 5-ጂ የኢንተርኔት ኔትወርክ አገልግሎት አስጀምሯል።

በማስጀመሪያ ስነስርዓቱ ላይ የፌደራልና የክልል የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ ከአምስት ወራት በፊት 5-ጂ የኔትወርክ አገልግሎትን በአዲስ አበባ ተግባራዊ በማድረግ ኢትዮጵያን ከዓለም ጥቂት አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

5-ጂ ኔትወርክ ዓለማችን የደረሰበት ፈጣን የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በተቀረጸው ስትራቴጂ መሰረት ኢትዮጵያን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል።

ይህ ዓለም የደረሰበት የመጨረሻው የቴክኖሎጂ ውጤትም የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና መሰል ዘርፎችን አገልግሎት በማሳለጥ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በአዳማ ከተማ ይፋ የሆነው ቴክኖሎጂም አዳማን ስማርት ሲቲ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማገዝ ሁነኛ የመፍትሄ አካል እንደሚሆን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከተሞች እና ተቋማት ዲጂታል አገልግሎትን እንዲያሳልጡ ኩባንያው ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የአምስተኛው ትውልድ የ5-ጂ ኔትወርክ ከአራተኛው ትውልድ 4-ጂ አገልግሎት አንፃር ሲታይም በአስራ አራት እጥፍ የሚልቅ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

ኩባንያው 68 ሚሊየን ደንበኞች እንዳሉት ጠቅሰው፤ በዚህም የደንበኞቹን ቁጥርና ፍላጎት በማሳደግ በዓለም አቀፍ ደረጃ 23፤ በአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም ይህንኑ ዓለም የደረሰበት የኔትወርክ አገልግሎት በሌሎች ከተሞች ለማስጀመር እየተሰራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል።

የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ ኃይሉ ጀልዴ፤ ባለፈው ዓመት የ4-ጂ አገልግሎት መጀመሩን ገልጸው፤ በዚህ ዓመትም ኢትዮ-ቴሌኮም አዳማ ከተማን የአምስተኛውን ትውልድ የ5-ጂ ኔትወርክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንድትሆን በማድረጉ  እድለኞች አድርጎናል ብለዋል።

ቴክኖሎጂው የአዳማ ከተማን ዘመናዊ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚያግዝ በመጠቆም የከተማዋን ስማርት ሲቲ ፕሮጀክት እውን ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያንም የ5-ጂ አገልግሎት መጠቀም የሚችል የሲም ካርድ እና የሞባይል ቀፎ በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችሉ በዚሁ ወቅት ተገልጿል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም