አድናቆት የተቸረው የሠላም ስምምነት

29

ትናንት የዓለም ሠላም ወዳድ ህዝቦች፣ ፖለቲከኞች እና የብዙኃን መገናኛዎችን ትኩረት የሳበው ጉዳይ በርካቶችን ለሰዓታት ያቁነጠነጠ ነበር።

የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር መምሪያ ትናንት 10 ሰዓት ላይ በአፍሪካ ኅብረት የአወያይ ቡድን በፕሪቶሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ አሳውቆም ነበር።

የተጠበቀው ጋዜጣዊ መግለጫ በተባለው ሰዓት ሳይሰጥ ቀርቶ ለሦስት ሰዓታት ተራዘመ። ይሄኔ ነበር ሚዲያውም ፖለቲከኛውም ያገባኛል ባዩውም የመሰለውን ሃሳብ ሲያነሳና ሲጥል ያመሸው።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ደም ሲያፋስስ የነበረው ጦርነት ለመቋጨት በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ለሣምንት ያልህ በደቡብ አፍሪካዋ ፕሪቶሪያ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው ውይይት በአንዳንዶች ዘንድ ‘ፍሬ አልባ ሆኗል’ ወደሚል ድምዳሜ ሲገፋ ተስተውሏል።  

ዳሩ ግን ‘አይሆንምን ትተሽ ይሆናልን ባሰብሽ’ ሆነና ነገሩ በ85 ዓመቱ አዛውንት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ የተመራው የአፍሪካ ኅብረት የአወያዮች ቡድን ዓለም እና ሚዲያው ያለጠበቀውን የምስራች ይዘው ከተፍ አሉ።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ጦርነትን ለማስቆም በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ውጤታማ ውይይት ተካሂዶ የሠላም ስምምነት እንደሚፈረም ይፋ አደረጉ።

ተደራዳሪ ወገኖች ገና የሥምምነት ፊርማቸውን ሳያሳርፉ ሚዲያ በሰበር ዜና ይተራመስ ያዘ። ቢቢሲ “አስገራሚ ሥምምነት” (a surprise deal) ሲለው ሮይተርስ ደግሞ “አስደናቂ ዲፕሎማሲያዊ እመርታ” (a dramatic diplomatic breakthrough) ሲል ሥምምነቱን አሞካሽቶታል። በናይሮቢ የሚታተመው ዴይሊ ኔሽንም ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ‘በአስደናቂ ሁኔታ’ ተቋጭቷል ሲል ዘግቧል።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት 'አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል' በሚል ርዕስየመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉን ጠቅሶ ዘገባውን የጀመረው ደግሞ ቢቢሲ አማርኛ ነው። ዘገባው ሲቀጥል ለቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት የተጠናቀቀው የሠላም ስምምነት ዘላቂ ሠላምን የሚያመጣ እና የትግራይን ሕዝብ መሠረታዊ ችግር የሚፈታ መሆኑን ጠቅሶ፤ በሠላም ንግግሩ የፌዴራል መንግሥቱ እና የህወሓት አመራሮች ግጭት ማቆምንና የህወሓት ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታትን ጨምሮ በ12 ነጥቦች ላይ ከስምምነት ላይ መደረሱን አውስቷል።  

በጥብቅ ምስጢራዊነት ለሣምንት ያህል ሲካሄደ የቆየው ውይይት በስኬት ተጠናቆ ተደራዳሪ ወገኖች ስምምነታቸውን በፊርማቸው አጸኑ። የሠላም ተስፋ ለኢትዮጵያ ፈነጠቀ። ዓለምም ሚዲያውም ተደመመ።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት በውይይት እንዲቋጭ ግፊት ሲያደርግ ከነበረው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም አዎንታዊ ምላሽ አስገኝቷል። የዓለም አገራት መሪዎችም ሥምምነቱን ግጭቱን ለማስቆም ገንቢ እርምጃ ሲሉ አወድሰውታል።

ሥምምነቱ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እስከ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ከአሜሪካው ነጩ ቤተ-መንግሥት እስከ አንካራ፣ ከአውሮፓ ኅብረት እስከ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-ምንግሥታት (ኢጋድ) ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስከ ሩሲያ እንዲሁም ከጎረቤት አገር ጅቡቲ እስከ ፈረንሣይ፣ ከሴኔጋል እስከ ካናዳ ያሉ አገራትና መሪዎች አድናቆት ተችሮታል። 

በተለይ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሥምምነቱ "ለሠላም አንድ አስፈላጊ እርምጃን ይወክላል" ሲሉ ገልጸውታል። “ሁለቱ ወገኖች እዚህ ስምምነት ላይ ለመድረስ ለሠላም ያላቸውን ቁርጠኝነት እናደንቃለን። አሜሪካ በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን ሂደት እና ሠላም ለመደገፍ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን አጋርነቷን አጠናክራ ትቀጥላለች” ሲሉም ኔድ ፕራይስ አረጋግጠዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሳሞይ ሩቶም ስምምነቱ እንደተፈረመ ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት የእንኳን ደስ ያላቹህ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ኬንያ በቀጣይ የኢትዮጵያን የሠላም ሂደትን ለመደገፍ ቁርጠኛ ናት ብለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የተደረሰው ስምምነት “የበርካታ ኢትዮጵያውያን ህይወት እና ንብረት የጠፋበትን ጦርነት ለማስቆም ወሳኝ እርምጃ” ሲሉ አድንቀውታል።

ይፋዊ የፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ መከናወኑን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሰጡት መግለጫ የሠላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ እና መንግሥታቸው ለሠላም ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጣቸው ደግሞ በሁሉም የብዙሃን መገናኛዎች በሚባል ደረጃ ሰፊ ትኩረት ያገኘ አዎንታዊ አቋም ሆኖ ተንጸባርቋል።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ በአርባ ምንጭ ስታዲየም ተገኝተው ባደረጉት ንግግርበደቡብ አፍሪካ በነበረው የሠላም ውይይት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለድርድር አይቀርብም የሚለው በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ማግኘቱ ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰዉ እና የቆሰሉ ህልማቸው እውን የሆነበት ነው ሲሉ ስኬቱን ገልጸውታል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት የነበረው ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ የሠላም ስምምነቱ በር ከፋች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አገር ወዳዱ የትግራይ ህዝብ ለተግባራዊነቱ ዳግም አለኝታነቱን እንዲገልጽም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ በፕሪቶሪያ ያስተላለፉት መልዕክትም ለዘላቂ ስኬቱ የሁሉም ወገን ትብብር እንደሚሻ ነው። "አሁን ላይ የሠላም ሂደቱ ማብቂያ አይደለም፤ የተፈረመው የሠላም ስምምነት ተግባራዊ መሆን እንዲችል መሰረት የጣለ እንጂ” ማለታቸው ቀጣይ ሥራዎች በጥንቃቄ እና በትብብር ማከናወን እንደሚመገባ አመላካች ነው።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ ምድር እና ሰማይ በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ከፍል የሠላም ነፋስ መንፈስ ጀምሯል። የፈነጠቀውን የሠላም ተስፋ ዘላቂ እንዲሆን ግን የተደረሰው ስምምነት በጥብቅ ዲስፕሊን ተፈፃሚ ማድረግ ይገባል። ለዚህ ደግሞ የመላ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተለይም ሰፊው የትግራይ ህዝብ ገንቢ ሚና በስፋት የሚጠበቅ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም