ኢትዮጵያ እንደሀገር እንድትቀጥል ሀገራዊ ምክክሩ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው መሰረታዊ ጉዳይ ነው--ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እንደሀገር እንድትቀጥል ሀገራዊ ምክክሩ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው መሰረታዊ ጉዳይ ነው--ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ
ጎንደር (ኢዜአ) ጥቅምት 24/2015 ''ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ሀገራዊ ምክክሩ ቀዳሚ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ ጉዳይ ነው'' ሲሉ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ ተናገሩ፡፡
በብሔራዊ ምክክሩ የንግዱን ማህብረሰብ ተሳትፎና ሚና ለማጎልበት የሚያስችል መድረክ ዛሬ በጎንደር ከተማ ተጀምሯል።
በመድረኩ ላይ ኮሚሽነሩ እንዳሉት ምክክር የእውነት ፍለጋ ሂደት በመሆኑ ለኮሚሽኑ ተልዕኮ መሳካት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የግልና የጋራ ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
ኮሚሽኑ የአካታችነት፣ የአሳታፊነት፣የግልጸኝነትና የተአማኒነት እሴቶችን መርህ በማድረግ ሀገር ጸንታ እንድትቀጥል ሀገራዊና ታሪካዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሀገር በቀል እውቀትን መሰረት በማድረግ በእውቀትና በጥበብ የታገዘ ብሄራዊ ምክክር ከታችኛው እርከን ጀምሮ ለማካሄድ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ኮሚሽኑ እያደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
የምክክር ሂደቱ መሰረታዊ ውጤት በህዝብና በመንግስት ያለውን ማህበራዊ ውል የሚያድስና የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ለሀገራችን የሰላም ግንባታ ሂደት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ዶክተር ዮናስ አስረድተዋል።
በበርካታ የዓለም ሀገራት የተካሄዱ ምክክሮች ለሀገራቸው ሰላምና እድገት መሰረት የጣሉ መሆናቸውን አስታውሰው፤ በኢትዮጵያም ሀገራዊ ምክክሩ ሰላምን፣ አብሮነትንና አንድነትን ለማጠናከር ትልቅ ሚና አለው" ብለዋል።
የንግዱ ማህበረሰብ ለብሔራዊ ምክክሩ ተልዕኮ መሳካት በእውቀት፣ በሀሳብና በገንዘቡ ጭምር በመደገፍ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
"ሀገራዊ ምክክር የኢትዮጵያውያን አጀንዳ በመሆኑ የጋራ መግባባትን በመፍጠር ዘላቂ ሰላምና ልማት እውን ለማድረግ ወሳኝ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው ናቸው።
በአንድ ሀገር ውስጥ የሚፈጠር የሰላም እጦት ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ እንቅስቃሴ እንደሚያስተጓጉል የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በእዚህም በዋናነት የንግዱ ማህበረሰብ ተጎጂ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
"ሀገራዊ ምክክሩ በአካታችነት፣ ብቃት ባላቸው ባለሙያዎችና በገለልተኛ አካል የሚመራ በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ ለኮሚሽኑ ተልዕኮ መሳካት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ ነው" ብለዋል።
የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩ አቡሃይ በበኩላቸው፣ የምክክር መድረኩ የሀገሪቱን የፖለቲካ ስብራት የሚጠግንና የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደትን የሚያሳልጥ በመሆኑ የሁሉም አካላት ተሳትፎና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
"የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚሽን ለዘመናት ምላሽ ሳያገኙና መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች በማጥናትና በመለየት ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ትልቅ የሰላም መሳሪያ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ባዩህ በዛብህ በበኩላቸው "ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የሕዝቦችን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለማስቀመጥ ያግዛል የሚል እምነት እንዳላቸው" ገልጸዋል።
የጎንደር ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት "ኢኒሸቲቭ አፍሪካ" ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በእዚህ የምክክር መድረክ ላይ ከንግዱ ማህበረሰብ የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።