የተደረሰው የሰላም ስምምነት መላው ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ ያደረገ ነው-የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
የተደረሰው የሰላም ስምምነት መላው ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ ያደረገ ነው-የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚረዳና መላው ኢትዮጵያውያንን አሸናፊ ያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በመንግስትና በህወሃት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ የደስታ መግለጫ አውጥቷል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጉባኤው ከሁሉም በፊት አስቀድሞ የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ የራሱን ድርሻ ሲወጣ የቆየ ነው።
በዚህም በመንግስትና በህወሃት መካከል ግጭቱ ከመከሰቱ በፊት ጀምሮ ሁሉም አካሄድ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥልና ያለመግባባቶችን በንግግር መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሲመክር መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከዚህም ባለፈ ከሁሉም ቤተ እምነቶች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችን ስፍራው ድረስ በመላክ ሰላማዊ ንግግሮች እንዲደረጉ በጽኑ ከመስራታቸውም ባለፈ በጸሎትና በምህላ ላይ የቆዩ መሆኑን አንስተዋል።
ነገር ግን ባልተጠበቀ መንገድ ግጭት ተቀስቅሶ ብዙ መስዋዕትነት ያስከፈለ አሳዛኝ ክስተት መሆኑን በማስታወስ፤“አሁን ላይ በሁለቱም ወገኖች የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለህዝቡ እፎይታን የሚሰጥ በመሆኑ እጅግ ደስ ብሎናል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰላም በኢትዮጵያ በዘላቂነት እንዲሰፍን ጽኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን በማንሳት፣ በመጪው ጊዜያትም ጉባኤው በሀገር የሰላም ግንባታ ሂደትና በዜጎች አብሮነት ላይ በትጋት እንዲሰራ አስታውቀዋል።
ጉባኤው በሰላም ሂደቱ የአንበሳውን ድርሻ የወሰደውን የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርቧል።