የኢዜአ የሚዲያ ልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ አጀንዳዎችን ቀርጾ ለማቅረብ ጉልህ ድርሻ ያበረክታሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ የሚዲያ ልማት ሥራዎች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚገነቡ አጀንዳዎችን ቀርጾ ለማቅረብ ጉልህ ድርሻ ያበረክታሉ
ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሚዲያ ልማት ዘርፍ እያከናወናቸው የሚገኙት ስራዎች በአለም አቀፍ ደረጃ በሚዲያው ዘርፍ የኢትዮጵያን ገጽታ ሊገነቡ የሚችሉ አጀንዳዎችን ቀርጾ ለማቅረብ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ተገለጸ።
የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትና የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በኢዜአ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቹ በጉብኝታቸው እየተከናወኑ የሚገኙ የሚዲያ ልማት ስራዎችንና ምቹ የስራ አካባቢ የመፍጠር እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ወቅትም ኢዜአ እያከናወናቸው የሚገኙ የሚዲያ ልማት ስራዎችና ምቹ የስራ አካባቢ መፍጠር እንቅስቃሴዎች ለሌሎችም ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል።
በተለይም በተቋሙ የተገነባው የሚዲያ ኮምፕሌክስ ከተቋሙ ባለፈ እንደ ሀገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው የተጠቀሰው።
በዚህ ወቅት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ መረጃን ለህዝብ በማድረስ አንጋፋና ቀደምት የሆነው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እያከናወናቸው የሚገኘው የሚዲያ ልማት ስራዎች የሚያስደንቁ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢዜአ በዘመናዊ ሚዲያ ህንጻ ግንባታ ያከናወናቸው ስራዎችና የስቱዲዮ ግንባታ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚዲያው ዘርፍ የኢትዮጵያን ገጽታ ሊገነቡ የሚችሉ አጀንዳዎችን ቀርጾ ለማቅረብ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።
ኢዜአ የዜናና የዘጋቢ ፊልም ስራዎችን ለሌሎች መገናኛ ብዙሃን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ አቅም ገንብቷል ያሉት ዶክተር ለገሰ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት፣ የማስታወቂያ ድርጅቶችና የፊልም አዘጋጆች የተቋሙን ስቱዲዮ እንዲሁም የሚዲያ ልማት ስራዎችን በመጠቀም ለስራቸው ተደራሽነት አብርክቶው የበዛ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው ኢዜአ ከአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት የሚያስችለውን የመገናኛ ብዙሃን ልማትና የስቱዲዮ ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
መገናኛ ብዙኃን በአሁኑ ወቅት ምቹ የስራ ከባቢን ከመፍጠር ጎን ለጎን የሙያ ኮዶችን በማጠናከርና የኤዲቶሪያል ፖሊሲያቸውን ተፈጻሚነት በመቆጣጠር ለሀገር ግንባታ የሚያግዙ ስራዎች ማከናወን ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።