ሙስና እና ብልሹ አሰራርን የሚፀየፍ ትውልድ መፍጠር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው-የተቋማት ኃላፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ሙስና እና ብልሹ አሰራርን የሚፀየፍ ትውልድ መፍጠር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው-የተቋማት ኃላፊዎች
ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) ሙስና እና ብልሹ አሰራርን የሚፀየፍ ትውልድ መፍጠር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ተናገሩ።
መንግስት በያዝነው በጀት ዓመት እንደ ሀገር ሊፈቱ ከሚገባቸው ብልሹ አሰራሮች ውስጥ ሙስናን መታገል ዋና አጀንዳው እንደሆነ ገልጿል፡፡
ይሁን እንጂ በሀገሪቱ የሚስተዋለውን ሙስና እና ብልሹ አሰራር ለመታገል ትልቁ ስራ መሰራት ያለበት የሰው አዕምሮ ላይ እንደሆነ ይታመናል፡፡
በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነው ትውልድ መልካም ስነ-ምግባር የተላበሰና ሙስናን የሚፀየፍ ከሆነ አገራዊ ግብን ማሳካት አዳጋች አይሆንም፡፡
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሀፊ ሊቀ-ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የሃይማኖት ተቋማት እንደ ቤተ-እምነታችን አስተምህሮ በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ ዜጋ የማፍራት ሀገራዊ ሃላፊነት አለብን ብለዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ ተገኘ ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች ያጋጠሟት ፈተናዎች የሚያሳዩት ትውልዱን በታማኝነትና በቅንነት አንፆ ማሳደግ ላይ ክፍተቶች እንዳሉበት ነው ፡፡
የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ተጋግዘን መስራት አለብን ነው ያሉት።
ወላጆች እና ትምህርት ቤቶች ትውልድን የማነጽ ትልቅ የቤት ስራ እንዳለባቸው የተናገሩት፤ የቪዥን ኢትዮጵያ ኮንግረስ ፎር ዲሞክራሲ ዳይሬክተር አቶ ታደለ ደርሰህ ናቸው፡፡
በዚህም የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ግብረ-ገብ፣ ታታሪና ሙስናን የሚጸየፍ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሚና ልናበረክት ይገባልም ብለዋል፡፡