በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነትና ጥፋት እንዳይከሰት ለተገባው የሰላም ቃል ተፈጻሚነት ኢትዮጵያዊ የዜግነት ሚናችንን ልንወጣ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዳግም ጦርነትና ጥፋት እንዳይከሰት ለተገባው የሰላም ቃል ተፈጻሚነት ኢትዮጵያዊ የዜግነት ሚናችንን ልንወጣ ይገባል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጥቅምት 24 ቀን (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያውያን ዳግም ወደ ጦርነት እንዳይገቡ በደቡብ አፍሪካ ለተደረሰው የሰላም ስምምነት ተፈጻሚነት ኢትዮጵያዊ የዜግነት ሚናችንን ልንወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርባ ምንጭ ስታዲየም ባደረጉት ንግግር በደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው ሀሳቦች በሙሉ ተቀባይነት ማግኘታቸውን አብስረዋል።
ከኢትዮጵያ ድሎች መካከልም የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለድርድር አይቀርብም፤ በአንድ ሀገር ከአንድ መከላከያ በላይ አያስፈልግም የሚሉት በሁለቱም ወገን ተቀባይነት አግኝቷል ነው ያሉት።
ይህም ለኢትዮጵያ አንድነት የሞቱና የቆሰሉ ጀግኖች ትግል ፍሬ በማፍራቱና ህልማቸውም ዕውን በመሆኑ ምስጋና ችረዋል።
ሕጋዊነትን ማስፈን ለአንድ ሀገር ህልውና መሰረት በመሆኑ በትግራይ ክልል የተካሄደው ሕገ ወጥ ምርጫ ተሰርዞ በህጋዊ ምርጫ እንዲተካ የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን አብራርተዋል።
በአንዳንድ ቦታዎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካራካሪ ቦታዎች በሰላም፣ በንግግርና በሀገሪቱ ሕግ ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ ሁለቱ ወገኖች መተማመናቸውንም አንስተዋል።
የተገኘው የሰላም ድል ለኢትዮጵያ ታላቅ ዕድል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ጠላቶች ግን በተገኘው የሰላም ድል አፍረዋል ብለዋል።
ጀግንነት ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከድል በኋላ የሚንጽባረቅ ደግነትና ይቅርታም ጭምር እንደሆነ ገልጸው፤ የትግራይን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ወንድምና እህቱ ጋር እንዲለማም በትጋት እንሰራለን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ኢትዮጵያዊ ጀግንነታችን የሚረጋገጠው ካለን አካፍለን በትግራይ የተጎዱ ወገኖች ማጉረስ ስንችል በመሆኑ፤ ሁሉም ህዝብና ዜጋ ካለው ለግሶ፣ በፍቅር ኢትዮጵያዊነትን ማላቅ እንደሚገባው ጠይቀዋል።
ለሀገር አንድነት ህይወት ከከፈልን፤ ደም ካፈሰስን ለሀገር አንድነትና ዕድገት ላባችንን አፍስሰን ፀጋና በረከቷን ማብዛት ይገባናል ብለዋል።
በጦርነቱ መከፈል የሌለበት ዋጋ መከፈሉን፣ ሀብትና ንብረት መውደሙን፣ ኢትዮጵያም በሚያውቋትም በማያውቋትም የዓለም ሚዲያዎች ክፉኛ ስትንጓጠጥ መክረሟን ጠቅሰው፤ ይህ ሊበቃ ይገባል ብለዋል።
መንግስት ለሰላም ልቡን ከፍቶ መቅረቡን የገባውንም ቃልም ለመጠበቅ ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ከሰላም ንግግር ማግስት በአብዛኛው ሸፍጥ፣ ተንኮልና ሸር እንደሚበዛ አስታውሰው፤ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በመሆን ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
እስከአሁን ከደረሰው ጥፋት በመማር ጥቂቶች በሚሸርቡት ሴራና ተንኮል መጠለፍ እንደማይገባ ጠቁመው፤ ዳግም የእርስ በርስ ጥፋት እንዳይከሰት ዜጎች ኢትዮጵያዊ፣ ህዝባዊ እና ዜግነታዊ ሚናቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል።
ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ በማናከስ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሰሩ ለቆዩ የቅርብና የሩቅ ጠላቶች ኢትዮጵያውያን እያሉ እትዮጵያን ማፍረስ፣ በቅኝ ቅዛት እሳቤ መግዛትም እንደማይችሉ ገልጸዋል።
ይልቁኑም ኢትዮጵያ የምትበለጽግ፣ ጽኑ፣ የአፍሪካ ኩራትና ፈርጥ ሆና እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ጥቂት አገራት ደግሞ ለኢትዮጵያ ህልውና ከጎኗ በመቆም ላሳዩት አጋርነት ኢትዮጵያ ታሪክ የምትሰራና ውለታ የማትረሳ አገር በመሆኗ ብድራቷን እንደምትከፍል ተናግረዋል።
ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ወኔና ጀግንነት ምልክት መሆኑን በማንሳት፤ "በእናንተ መቁሰል፣ መጎዳትና የሕይወት መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አንድነቷን በማስከበሯ ኮርተንባችኋል" ነው ያሉት።
‘ጀግኖች ሞታችሁ ሞት አይደለም የደማችሁ መፍሰስም የደም መፍሰስ አይደለም የኢትዮጵያ መጽናት ነውና እንወዳችኋለን እናከብራችኋለን ‘ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።