ቀጥታ፡

ሰራዊቱ ለሀገር የከፈለውን ዋጋ ስንዘክር የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል-የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች

ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) ሰራዊቱ ለሀገር የከፈለውን ዋጋ ስንዘክር የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ብልጽግናዋን በማረጋገጥ ሊሆን እንደሚገባ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ።

በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የደረሰው ጥቃት ዳግም እንዳይከሰት ትውልድ ሊማርበት እንደሚገባም አክለዋል።  

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ የተካሄደው ጅምላ ጭፍጨፋና ጥቃት በተለያዩ ተቋማት ዛሬ ታስቦ ውሏል።

ቀኑን የሠላም ሚኒስቴር፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ አስበውታል።    

መርሃ-ግብሩ "ስለ ኢትዮጵያ የከፈላችሁትን አንረሳም" በሚል መሪ ሀሳብ የተከናወነ ሲሆን በጥቃቱ የተሰዉ እና ጉዳት የደረሰባቸው የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የሚዘክር የጧፍ ማብራትና ሌሎች ዝግጅቶች ተካዷል።

የሠላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም፤ በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ጥቁር አሻራ ጥሎ ያለፈና የትኛውም ትውልድ ሊደግመው የማይገባ ነው።

ዛሬ ቀኑን የምናስበው ቀጣዩ ትውልድ በተመሳሳይ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ እንዳይጓዝ ትምህርት እንዲሆነው ነው ሲሉም አክለዋል።

ቀኑ መከለከያ ሰራዊቱ በየዘመናቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ለሚከፍለው ዋጋ ክብራችንን የምንገልጽበት ሊሆን እንደሚገባ ነው ሚኒስትሩ አጽንኦት የሰጡት።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ለሰላም መረጋገጥ ከሚከፍለው መስዋዕትነት ጎን ለጎን ሰላምን በዘላቂነት ለመገንባት ከሁላችንም የሚጠበቅ ድርሻ መኖሩን መገንዘብ ያሻል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚታሰበውን ብልጽግና ለማረጋገጥ፣ ግጭት እንዳይኖር እንዲሁም ዜጎች ከቦታ ቦታ ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን እንስራ ሲሉም ነው ሚኒስትሩ ጥሪ ያቀረቡት።   

በሰራዊቱ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የምናስበው የተፈጠረውን ቁስል ለማስታወስ ሳይሆን በቀጣይ ትምህርት እንዲሆነን ነው ሲሉ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሩ ቴዎድሮስ በቀለ ተናግረዋል።

ክስተቱ መቼም ቢሆን የማይረሳና በየዘመናቱ ሊታወስ የሚገባ መሆኑን ጠቁመዋል።

የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና ሰራዊቱ ላይ የተፈጸመው ድርጊት መላው ኢትዮጵያውያንን ያሳዘነ መሆኑን አስታውሰዋል።

እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ አሸነፊ ሆናለች ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የሰነበተው የሠላም ንግግር የኢትዮጵያን ጥቅምና ሉዓላዊነትን ባስጠበቀ መልኩ መጠናቀቁ ለዚህ ማሳያ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው፤ ሰራዊቱ የከፈለው መስዋዕትነት መና እንዳልቀረ በደቡብ አፍሪካ የተካሄደው የሰላም ስምምነት ህያው ምስክር ነው።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሞክር የትኛውም ኃይል ህልሙ እንደማይሳካ ህዝቡና መከላከያ ሰራዊቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጋራ በከፈሉት መስዋዕትነት ማረጋገጥ መቻላቸውን ነው የጠቀሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም