ኢትዮጵያ ሁሌም ችግሮቿን በአሸናፊነት ተሻግራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ሁሌም ችግሮቿን በአሸናፊነት ተሻግራ ትቀጥላለች
ጋምቤላ ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ሁሌም ችግሮቿን በአሸናፊነት ተሻግራ እንደምትቀጥል ተገለጸ።
ጥቅምት 24 መቼም አንረሳውም በሚል መሪ ሃሳብ በጋምቤላ ክልል በፓናል ውይይት፣ በሰልፍ ትርኢት፣ በሻማ ማብራትና ሌሎች ዝግጅቶች ታሰቦ ውሏል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ጁል ናንጋል እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ሁሌም ችግሮቿን በአሸናፊነት እየተሻገረች ያለው፤ የሀገርን ዳር ድንበርና ሰላም ለማስጠበቅ በሚዋደቁ ጀግኖች ልጆቿ የዓላማ ጽናትና በህዝቦቿ የጋራ አንድነት መሆኑንም ተናግረዋል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ሲጠብቃቸው በነበሩት ወገኖቹ ተከድቶ የተፈጸመበት ጥቃት መቼውንም የማይዘነጋ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ፒተር አማን በበኩላቸው፤ ጥቅምት 24 በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ድርጊት በኢትዮጵያውያን ዘንድ መቼውም የማይዘነጋ መጥፎ ታሪክ ነው ብለዋል።
የክልሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደምና አጥንቱን በመከስከስ የኢትዮጵያን ሰላምና ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሲል መስዋትነት እየከፈለ ላለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሁለንተናዊ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የክልሉ የሃይማኖት አባቶች የጋራ ምክር ቤት ተወካይ ቆሞስ አባ መላክ ሳህለማሪያም በመረሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጥቅምት 24 በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የደረሰው ጉዳት በሃይማኖት ተቋማት በጸሎት ሲታሰብና ሲዘከር ይኖራል ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማቱ ዛሬም ሆነ ነገ ከመንግስት ጎን በመሆን የሀገርን ዳር ድንበር ለሚጠብቀው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጸሎት እንደሚደግፉ ተናግረዋል።
በመታሰቢያ መረሃ ግብሩ ላይ ኢትዮጵያ በእናንተ ጽኑ ክንድ ጸንታ ትኖራለች!፤ መከላከያችን ሃይላችን መከታችን ነው!፤ መከላከያ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዋስትና ነው! ፤ ዘላለማዊ ክብር ለሰሜን ዕዝና ሌሎች መሰል መፈክሮች በመረሃ ግብሩ ታዳሚዎች ተስተጋብተዋል።