ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት በማስጠበቅ ለዘላቂ ሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል- ዶክተር አብርሃም በላይ

ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ሰላም እና ግዛታዊ አንድነነት በማስጠበቅ ለዘላቂ ሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ።

የመከላከያ ሚኒስቴር ጥቅምት 24  ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ የሰራዊት አባላት ላይ የተፈጸመውን የግፍ ጭፍጨፋ ሁለተኛ ዓመት "መቼም አንረሳውም" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ መርሃ ግብሮች አስቧል።

ዶክተር አብርሃም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በሰራዊቱ ላይ ጨለማን ተገን በማድረግ ከጀርባ የተፈጸመበት ጥቃት ጭካኔና ክህደት የታየበት ነው።

ዕለቱ ሲዘከር በመጥፎ ትውስታ ብቻ ሳይሆን የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ የተፈጸመበትን ክህደት ቀልብሶ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ሀገርን ያፀናበት ትልቅ ድልም በኩራት ይነሳል ብለዋል።

ተቋማዊ ጥንካሬን በመገንባት ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ  የመከላከያ ሰራዊት መገንባት መቻሉንም ሚኒስትሩ ጨምረዋል።

ክስተቱ ዳግም እንዳይፈጸምና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ሰላም እንዲሰፍን በአዲስ ዕይታ፣ በሙሉ ተስፋና አስተሳሰብ እንዲሁም በፍቅርና ይቅርታ ለመጓዝ መሰረት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ሠራዊቱ በአሁኑ ወቅት የትኛውንም ኢትዮጵያን ለመዳፈር የሚሞክርን ኃይል በሚመክትበት አስተማማኝ ቁመና ላይ ነው ብለዋል።

ሠራዊቱ በአራቱም ማዕዘን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት በማስጠበቅ የዘላቂ ሰላም ዘብነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ያነሱት።

ኢትዮጵያውያን ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት የመፍታት ሂደትን በመደገፍ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የበኩላቸውን እንዲወጡም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን የሚመጥን ዘመናዊና ጠንካራ የመከላከያ ኃይል እየተገነባ  መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ሁለተኛ ዓመት 'መቼም አንረሳውም' በሚል በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ታስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም