ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ልማታችንን ማፋጠን ይጠበቅብናል -የውሀ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር

ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የሀገሪቱን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ልማታችንን ማፋጠን ይጠበቅብናል ሲሉ የውሀ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች ተናገሩ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች ጥቅምት 24 ቀን በ2013 በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን የክህደት  ጥቃት ሁለተኛ ዓመት ”ስለኢትዮጵያ የከፈላችሁትን አንረሳም ” በሚል መሪ ቃል ዘክረዋል።

የሚኒስቴሩ ሠራተኞች እንደተናገሩት፤ የሀገር መከታ በሆነው የሰሜን እዝ ላይ የተፈፀመው ጥቃት አሳዛኝና በየትኛውም ዓለም ያልታየ ነው።

ዕለቱን ስንዘክርም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የሕይወት መስዋእትነት የከፈለውን ጀግና  ሰራዊት በማሰብ እና ደጀንነታችንን በማሳየት  ነው ብለዋል።

ሠራተኞቹ አክለውም የኢትዮጵያ መንግስትና ሕወሃት ትናንት በደቡብ አፍሪካ የተፈራረሙት የሰላም ስምምነትም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ትልቅ በር የከፈተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እኛም ለሀገራችን ሰላምና ለኢኮኖሚያዊ እድገቷ መረጋገጥ በየተሰማራንበት መስክ በትጋት እንሰራለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም