ቀጥታ፡

በጀግኖች የተከበረውን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በኢኮኖሚያዊ ልማት ለማጽናት በርትተን መስራት አለብን- ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ

ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) በጀግኖች መስዋዕትነት የተከበረውን የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በኢኮኖሚ ልማትም ለማፅናት ሁላችንም ቆርጠን መነሳት አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የሥራ ኢንተርፕራይዝ፣ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር ዓባይ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት ሁለተኛ ዓመት 'ጥቅምት 24ን መቼም አንረሳውም' በሚል መሪ ቃል አስቧል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ  ኩራት መሆኑን በአህጉሪቱ ሰላም ማስከበር  ያሳየው ተጋድሎ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዘብ የሆነውን መከላከያ ሰራዊት ከጎኑ በመቆም ማመስገን እንደሚገባ ገልፀው በሠራዊቱ ላይ የተፈጸመበት ክህደት እንዳይደገም መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጠየቁት ምክትል ከንቲባው አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን ከድህነት እንድትወጣ ለማስቻል ብርቱ ጥረት ማድረግ አለብን ብለዋል።

በዚህም ኢትዮጵያን ከልመና የማላቀቅና ኢኮኖሚያዊ ነጻነትን የማረጋገጥ ግብን ማሳካት እንደሚገባ በማመላከት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም