ቀጥታ፡

የሰላም ውይይቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ ብሄራዊ ጥቅምና ዘላቂ ሰላም ማረጋገጡ ትልቅ ድል ነው - የደቡብ ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት

ሐዋሳ፣ ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሰላም ውይይቱ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ ብሄራዊ ጥቅምና ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ አግባብ መጠናቀቁ ትልቅ ድል መሆኑን የደቡብ ክልል ብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ አስታወቁ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ለመዘከር ለሰራዊቱ ድጋፍ እና ደም በመለገስ በክልሉ ታስቧል።

"ጥቅምት 24 አንረሳውም" በሚል መሪ ሃሳብ የደቡብ ክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች በርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ተገኝተው በጋራ አስበውታል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜ እንደገለጹት፤ በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የቆየው የሰላም ውይይት የኢትዮጵያን ሉአላዊነት፣ ብሄራዊ ጥቅምና ዘላቂ ሰላም በሚያረጋግጥ አግባብ መጠናቀቁ ትልቅ ድል ነው።

ድሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትና የፀጥታ ሃይሉ፣ ድሉ የመላ ኢትዮጵያዊያንና የክልሉ ህዝቦች ድል መሆኑንም ገልጸዋል።

የጀግንነትና የሉአላዊነት ምልክት ተደርጎ በሚቆጠረው መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት ክህደት መፈፀሙን አስታውሰዋል።

ቀኑን ስንዘክር የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመጠበቅ መስዋእትነት እየከፈለ የሚገኘውን መከላከያ ሰራዊት ከታሪክ ጋር በማስተሳሰር ለበለጠ ዝግጁነት እንዲነሳ ድጋፍ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ህዝቡ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ደጀንነት አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አፈ ጉባኤው፤ ሰራዊቱ ከውጭ ጠላት ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ባንዳ ሃገሪቱን ለመጠበቅ እያደረገ ላለው መስዋእትነት እውቅና መስጠት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ጥቃት የተፈጸመበት ሰራዊቱ ከህዝቡ ጋር ጠንካራ ትስስር ያለው የአገር ዘብ እና የልማት ሃይል እንደሆነ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በመከላከያ ሰራዊት መስዋእትነት የከፍታ ጉዞዋን እያረጋገጠች ነው ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ የመከላከያ ሰራዊቱን አቅምና ውጤታማነት የሚያረጋግጥውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በፕሮግራሙ ከታደሙት መካከል አቶ ቸርነት ፍቃዱ ጥቅምት 24ን የማይረሳ የሚያደርገው ለኢትዮያዊያን ደጀን የሆኑ ሰራዊት አባላት ላይ የተፈፀመ በደል መሆኑን ተናግረዋል።

ቀኑ በሌላ ድል መታሰቡ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው፤ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ብስራትና አሸናፊነት የተረጋገጠበት ነው ብለዋል።

በሀገር ጉዳይ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብ ገንዘቡንና ልጁን ጭምር የሃገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ሲሰጥ መቆዩቱንም ተናግረዋል።

የተደረገው የሰላም ውይይት ጦርነትን በሚያስቆም መልኩ ከስምምነት በመደረሱ ሁሉም ወደ ልማት ፊቱን ሊያዞር ይገባል ብለዋል።

የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል አባል  ኮንስታብል ብርሃኑ ሃይሌ በበኩሉ ለአገሩ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ኢትዮጵያ በሰራዊቱና በመላ ህዝቡ አንድነት ተከብራ እንደምትኖር ገልጾ፤ ህዝቡ በመካላከያ ሰራዊቱ ላይ የደረሰውን በደል ለማሰብ እያደረገ ስላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም