ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአርባምንጭ እስታዲየም ያደረጉት ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአርባምንጭ እስታዲየም ያደረጉት ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች
-የተከበርከው የትግራይ ህዝብ እኛ ልባችንን ከፍተን ሰላም ለማምጣት ዝግጁ ስለሆንን፤ የገባነውን ቃል ለመጠበቅ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በጋራ በመሆን የበኩልህን ሚና እንድትወጣ ተንኮል፣ክፋት ሸር እዚህ ጋር እንዲበቃ ጥቂቶች እየሸረቡ ኢትዮጵያውያንን ዳግም አደጋ ውስጥ እና ጦርነት ውስጥ እንዳያስገቡ ህዝባዊ፣ ኢትዮጵያዊና የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ ለትግራይ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በታላቅ ትህትና አደራ ማለት እፈልጋለሁ።
- ኢትዮጵያውያን ተጣልተዋል ይገዳደላሉ ገንዘብ ፣ ሚዲያ ና የጦር መሳሪያ ብናቀብል ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብላችሁ ብዙ የተጋችሁ የቅርብ እና የሩቅ ሀገራት ኢትዮጵያ የማትፈርስ የጸናች የምትበለጸግ የአፍሪካ ፈርጥና ኩራት ስለሆነች ኢትዮጵያን ማፍረስም ማሳነስም በኮሎኒ መግዛትም የማይታሰብ ስለሆነ ስላወጣችሁት ወጪ፣ ስለ ድካማችሁ፣ ስለ ልፋታችሁ ፈጣሪ ይቅር ይበላችሁ ልል እወዳለሁ።
-በዚህ የጭንቅ ግዜ ኢትዮጵያን አንጥልም ብለው ጥቂት ሀገራት ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክልል ሆነው በመከራ በችግር በጫና ከኛ ጋር መቆማቸው ብቻ ሳይሆን ያላቸውን ያካፈሉ ጓዳችንን ያበሱ ጥቂትም ቢሆኑ አስደማሚ ወዳጆች እንዳሉን ያየንበት ግዜ ስለሆነ ለነሱ ኢትዮጵያ ታሪክ የምትሰራ ታሪክ የማትረሳ ሀገር ስለሆነች ብድራታችሁን የምትከፍል መሆኑን እና ታላቅ ምስጋና እንዳላት ልገልጽላችሁ እወዳለሁ።
አንተ የተከበርክ ለህይወትህ የማትሳሳ በብርድ በዝናብ በየጫካው የተኛህ አንተ የኢትዮጵያ ኩራት የሀገር መከላከያ ሠራዊት አንተ የኢትዮጵያ ወኔ አንተ የኢትዮጵያዊነት ምልክት አንተ የጀግንነት ምልክት ባንተ ድካም ባንተ መቁሰል ባንተ ህይወት ኢትዮጵያ ዳግም ቆማ በክብር መናገር ስለቻለች መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገር መከላከያ ያለንን ታላቅ አክብሮት እና ፍቅር ካለንበት ቆመን እናሰማለን።
- ሰው ይፈጠራል ይኖራል ይሞታል ጀግና ግን ይፈጠራል ለልጆቹ ሀገር ያጸናል እሱ መሰዋዕት ይሆናል እናንተ ጀግኖች ሞታችሁ ሞት አይደለም የደማችሁ መፍሰስም የደም መፍሰስ አይደለም እንወዳችኋለን እናከብራችኋለን ክብር ምስጋና ለተሰው ሰማዕታት እንዲሆን የተቀራችሁ ክብር እንዲሰማችሁ ለመግለጽ እወዳለሁ።
-የጋሞ ሽማግሌዎች እንደሚታጨደው ሳር ሳይሆን እንደሚበቅለው ሳር ያለምልምህ ይላሉ፤ ኢትዮጵያ እንደሚታጨደው ሳር ሳይሆን እንደሚበቅለው ሳር የምትለመልም የምትበለጽግ የአፍሪካ ኩራት የሆነች የሁላችን መታፈሪያ ብርቅዬ በመሆኗ የዚች ሀገር ዜጋ መሆን ትልቅ ክብር ነው።
- ከኛ የተለየ የፖለቲካ እሳቤ ያላችሁ ግለሰቦች፣ቡድኖች በተከበረው የጋሞ ህዝብ ፊት ጥሪ ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ አንኳን በአንድ ሀገር በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ብዙ የማያግባቡ ጉዳዮች አሉ እንከራከር እንነጋገር እንወያይ ግን የኢትዮጵያን ጥቅም ለታሪካዊ ጠላቶቿ አሳልፈን የምንሰጥ ባንዳዎች አንሁን።