ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዳግም በክብር ቆማ እንድትራመድ ያደረገው ጀግናው ሰራዊት ታላቅ ክብርና ምስጋና ይገባዋል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

ጥቅምት 24/2015/ኢዜአ/ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህይወት ዋጋ ከፍሎ ኢትዮጵያን ዳግም በክብር ቆማ እንድትራመድ ስላደረገ ታላቅ ክብርና ምስጋና ይገባዋል አሉ።

ሰራዊቱ የኢትዮጵያ ወኔና ጀግንነት ምልክት መሆኑን በማንሳት፤ "በእናንተ መቁሰል፣ መጎዳትና የህይወት መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ሉዐላዊ አነድነቷን በማስከበሯ ኮርተንባችኋል" ነው ያሉት።

‘ጀግኖች ሞታችሁ ሞት አይደለም የደማችሁ መፍሰስም የደም መፍሰስ አይደለም የኢትዮጵያ መጽናት ነውና  እንወዳችኋለን እናከብራችኋለን ‘ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም፤ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ብለው ሲያሟርቱና ጫና ሲያደርጉ የነበሩ ሀገራት ሴራ መክሸፉን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የማትፈርስና በፅናት የምትገሰግስ ሀገር መሆኗን በየዘመኑ በማሳየት የአፍሪካ ፈርጥና ኩራት የሆነች ሀገር ናት ብለዋል።

እኛ እያለን ኢትዮጵያን ማፍረስም፣ ማሳነስም ሆነ በኢኮኖሚ መግዛት የማይታሰብ መሆኑን ጠላቶቿ ሊያውቁ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሞከሩ ሀገራትም ስላወጡት ወጪና ስለከንቱ ድካማቸው ይቅርታ አድርገንላቸዋል ነው ያሉት።

በአንጻሩ በጭንቅ ጊዜ  ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የታገሉ ጥቂት ሀገራትን ኢትዮጵያ በታሪኳ ከፍ ያለ ስፍራ በመስጠት ብድራታቸውን እንደምትከፍል ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ባለውለታዎቻችንን ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም