ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በመሬት ላይ ያስገኙትን ታሪካዊ ድል የሚያጸና የሰላም ድል ተመዝግቧል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በመሬት ላይ ያስገኙትን ታሪካዊ ድል የሚያጸና የሰላም ድል ተመዝግቧል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በመሬት ላይ ያስገኙትን ታሪካዊ ድል የሚያጸና የሰላም ድል መሆኑን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአርባ ምንጭ ስታዲየም ተገኝተው ለህዝብ በይፋ ባደረጉት ንግግር፤ በደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው ሀሳቦች መቶ በመቶ ተቀባይነት አግኝተዋል ብለዋል።
በስምምነቱም ኢትዮጵያ ያሸነፈችባቸው ድሎች መመዝገባቸውን አስታውቀው፤ የኢትዮጵያ ሉዑላዊነትና የግዛት አንድነት ለድርድር አይቀርብም የሚለው ነጥብ በሁለቱም ወገን ተቀባይነት አግኝቷል ነው ያሉት።
ይህም "ለኢትዮጵያ አንድነት የሞቱና የቆሰሉ ጀግኖች ትግላቸው ፍሬ በማፍራቱ እንኳን ደስ ያላቸው፤ ህልማቸው እውን በመሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል" ብለዋል።
በአንድ ሀገር ከአንድ መከላከያ በላይ አያስፈልግም የሚለው በሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ እንደተደረሰበት ጠቅሰው፤ ይህም ከፍተኛ ድል መሆኑን አንስተዋል።
ሶስተኛ ህጋዊነትን ማስፈን ለአንድ ሀገር ህልውና መሰረት በመሆኑ በትግራይ ክልል የተካሄደው ህገወጥ ምርጫ ተሰርዞ በህጋዊ ምርጫ እንዲተካ የሚለው ሀሳብ ተቀባይነት ማግኝቱን አብራርተዋል።
በአንዳንድ ቦታዎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው አካራካሪ ቦታዎች በሰላም፣ በንግግርና በሀገሪቱ ህግ ብቻ ምላሽ እንዲያገኙ በሁለቱም ወገኖች ትምምን ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።
ጀግንነት ማሸነፍ ብቻ እንዳልሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጀግንነት ከድል በኋላ የሚንፀባረቅ ደግነት ይቅርታም ጭምር መሆኑን አንስተዋል።
የተገኘው የሰላም ድል ታላቅ እድል መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም የኢትዮጵያ ጠላቶች አፍረዋል ነው ያሉት።
የትግራይን ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ወንድምና እህቱ ጋር እንዲለማም በትጋት ይሠራል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊ ጀግንነታችን የሚረጋገጠው ካለን አካፍለን በትግራይ የተጎዱ ወገኖቻችንን ማጉረስ ስንችል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ካለን አካፍለን ፍቅር ተሰጣጥተን ኢትዮያዊነትን ከፍ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለሀገር አንድነት ህይወት ከከፈልን ደም ካፈሰስን ለሀገር አንድነትና እድገት ላባችንን አፍስሰን ጸጋና በረከቷን ማብዛት አለብን ነው ያሉት።