ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለድርድር አይቀርብም-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ

ጥቅምት 24 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለድርድር አይቀርብም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ትላንት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ የተደረሰው ስምምነት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ሁለቱም አካላት ተስማምተዋል ብለዋል።

በትግራይ ክልል የተካሄደው ምርጫም ህገ-ወጥ መሆኑን ሁለቱም አካላት የተግባቡ በመሆኑ በአዲስ ምርጫ አስተዳደር እንዲመሰረትም ከስምምነት መደረሱን ነው የገለጹት።

ለሀገር ዘላቂ ሰላም እና ልማት እንዲሁም ኢትዮጵያ እፎይ እንድትል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተከፈለውን መስዋዕትነት በይቅርታ መሻገር ይገባል ብለዋል።

በሁሉም አካባቢ የማይገባ ዋጋ ተከፍሏል የሰው ህይወት አልፏል ንብረት ወድሟል ከዚህ በኋላ ዳግም ችግር ውስጥ እንዳንገባ በቂ አስታራቂ ሽማግሌዎች ያለን በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ሚናውን ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።

የትግራይ ክልል ህዝብም እንዲሁ የተደረሰው ስምምነት ገቢራዊ እንዲሆን የድርሻውን እንዲወጣ መልእክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ያልተገባ ጫና ለማሳደር የሚሞክሩ ስለሚኖሩ ህዝቡ በቃችሁ ሊላቸው ይገባልም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በገባችው ቃል መሰረት በችግሩ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመገንባት ጥረት ታደርጋለች" ለዚህም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም