አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን መመከቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን መመከቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል-ቋሚ ኮሚቴው
ጥቅምት 23/2015 (ኢዜአ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን መመከቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን የ2015 በጀት ዓመት መጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ዛሬ ገምግሟል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ፈትሂ ማህዲ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ቋሚ ኮሚቴው የአስተዳደሩን አፈጻጸም በጥልቀት በመገምገም ጥሩ የሚባል ክንውን መኖሩን ማረጋገጥ ችሏል።
አገራዊ ደህንነትን ለማረጋገጥ የለውጥ ስራዎች ከተካሄደባቸው ዘርፎች መካከል የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በተቋሙ ባደረገው የመስክ ምልከታ አስተዳደሩ ትልቅ እምርታ እያሳየ መሆኑን ገምግሟል ብለዋል።
ሆኖም ተቋሙ በእውቀት የታነጸ፣ ከጊዜው ጋር የሚራመድ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በዓለም ላይ የሳይበር ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን ያነሱት ዶክተር ፈትሂ አስተዳደሩ የሳይበር ጥቃቶችን መመከት ላይ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበትም አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ በበኩላቸው አስተዳደሩ የኢትዮጵያን ዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ቁልፍ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአብነትም ደህንነቱ የተጠበቀ "ደራሽ" የተሰኘ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት መዘርጋቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ግብር ከፋዩ ካለበት ሆኖ መክፈል የሚችልበት መሆኑንም አብራርተዋል።
ከዚህ ባለፈም አስተዳደሩ መረጃ መለዋወጫ /ዳታ ኤክስቼንጅ/ መሰረተ ልማት እየዘረጋ መሆኑን ያብራሩት አቶ ሰለሞን ይህም 50 በመቶ መጠናቀቁን አስረድተዋል።
እነዚህ መሰረተ ልማቶች በአገር ውስጥ መካሄዳቸው የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስቀሩም ነው ያነሱት።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ አስተዳደሩ በኤሮ ስፔስና መከላከያ በርካታ ውጤቶች ያስመዘገበ ሲሆን የመረጃ ጦርነት ላይም ቁልፍ ስራዎች ተከናውነዋል።
የሳይበር ደህንነቱን ለማስጠበቅ ተለዋዋጭ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንደሚያስፈልጉ ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የግዥ ሥርዓቱ ከዘርፉ ጋር አብሮ የሚጓዝ ባለመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ ገልጸዋል።