ስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ትምህርት ሚኒስቴር በሰው ሃብት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና ትምህርት ሚኒስቴር በሰው ሃብት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ተስማሙ
ጥቅምት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) የስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና የትምህርት ሚኒስቴር በሰው ሃብት ልማት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ዛሬ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እና የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በክህሎት ልማት ስራ ላይ ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ የዳሰሳ ጥናት ከተደረገ በኋላ የተደረገ መሆኑ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለፁት፤ ስምምነቱ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ወደ ኢንዱስትሪው ለሚቀላቀሉ ስራ ፈላጊዎች ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በተለይ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር ተሳስሮ በመስራት የስራ ፈጣሪነት አስተሳሰብ ማጎልበት እንደሚቻል ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
ከትምህርት ቤት ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ፈላጊ ዜጋ እንዳይሆኑ ስምምነቱ ፋይዳው የጎላ መሆኑንም እንዲሁ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ተቋማቸው በትምህርት ጥራት ዙሪያ እየሰራ ላለው ስራ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።
ከትምህርት ጥራት ጎን ለጎን የክህሎት ስራ ላይ የላቀ ውጤት ለማምጣት በጋራ ለመስራት ያግዛል ነው ያሉት።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ አክለውም በዕውቀትና ክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራት ጥራት ያለው ትምህርት ከመስጠት በተጓዳኝ የክህሎት ትምህርትም ትልቁ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።