ቀጥታ፡

የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ምን ጊዜም ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንሰለፋለን- የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች

አርባ ምንጭ፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማስከበር ምን ጊዜም ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንደሚሰለፉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።

የ2ኛ ዓመት ዝክረ ሰሜን እዝን በማስመልክት አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የከተማዋ ነዋሪ ኮማንደር ወልዴ ወተራ ሰሜን ዕዝ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስከበር በዘለለ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት የትግራይ ክልል ህዝብን አገልግሏል።

ሆኖም አሸባሪው ህወሓት ውለታውን በመዘንጋት በሰራዊቱ ላይ ክህደትና ጥቃት በመፈጸም በታሪክ የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ ማለፉን አስታውሰዋል።

በደሉ የማይረሳና የሚያሳዝን ቢሆንም ሀገራዊ አንድነትን ይበልጥ ማጠናከሩን ተናግረዋል።

በወቅቱ በተፈጸመው ድርጊቱ እንደ አንድ ዜጋ ጥልቅ ሀዘንና ቁጭት እንደተሰማቸው ገልጸው፤ ማንኛውም ጥቃት ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ሊያደፈርስ አይችልም" ብለዋል።

ከሰራዊቱ ጎን በመሰለፍ የሀገራችንን ሉዐላዊነት ለማስከበር በሚደረገው እንቅስቃሴ ለመሳተፍ ዝግጁ ነኝ ሲሉም አረጋግጠዋል።

`አንድነታችን በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባ በመሆኑ በትውልድ ቅብብሎሽ የሀገራችን ሉዓላዊነት እየተከበረ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሌላኛው የአርባ ምንጭ ነዋሪ አቶ ዓለማየሁ ዳኜ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ፈፅሞ የሀገር ፍቅር የሌለውና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን እያገለገለ የሚገኝ ባንዳ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው በደል የዚህ ድርጊቱ መገለጫ እንደሆነም አመልክተዋል።

ቡድኑ በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ምን ጊዜም አንዘነጋውም ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በደረሰበት ጥቃት ሳይበገር ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉአላዊነት ለማስከበር እያደረገ ላለው ተጋድሎ ልዩ አክብሮት እንዳላቸው ገልጸው፤ ለሰራዊቱ ያላቸውን ደጀንነት በተግባር እያሳዩ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሀገሪቱ ጠላቶች የቱንም ያህል ቢደክሙም ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር በመሆኗ ታሪኳና ክብሯ ለዘላለም ተጠብቆ ይኖራል ነው ያሉት።

ወይዘሮ መስከረም ኃብተገብርኤል በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት ከውጭ ጠላቶች ጋር በማበር ሀገር ለማፍረስ የሚያደርገው ጥረት እንደማይሳካ ገልጸው፤ አንድ ከሆንን ጠላትን እፍረት በማከናነብ የሀገራችን ዕድገት እውን እናደርጋለን ብለዋል።

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው አሸባሪውን ለመፋለም ህዝቡ ከአራቱም ማዕዘን ነቅሎ በመውጣት ለሉዓላዊነቱና ለክብሩ ሲል መዝመቱ ህያው ምስክር ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም