የሽብር ቡድኑ ሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው የሀገር ክህደት ተግባር በትውልድ ሲዘክር ይኖራል -በጎንደር ተመላሽ የሠራዊት አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የሽብር ቡድኑ ሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው የሀገር ክህደት ተግባር በትውልድ ሲዘክር ይኖራል -በጎንደር ተመላሽ የሠራዊት አባላት
ጎንደር፣ ጥቅምት 23/2015(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ታሪክ የማይረሳው የሀገር ክህደት ተግባር በትውልድ ሲዘከር ይኖራል ሲሉ በጎንደር ከተማ ከሠራዊቱ በክብር የተመለሱ አባላት ተናገሩ።
ህወሓት የመከላከያ ሠራዊት አስከሬን እንኳ በክብር እንዳይቀበር ያደረገ ጨካኝ የሽብር ቡድን መሆኑንም ተመላሽ የሠራዊት አባላቱ ተናግረዋል።
በጎንደር ከተማ የሚኖሩት መቶ አለቃ ቻለው አስማረ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የሽብር ቡድኑ በሠራዊቱ ላይ የፈጸመው ክህደትና የጭካኔ ተግባር ከሰብአዊነት ማፈንገጡን ብቻ ሳይሆን አረመኔነቱንም የሚያሳይ ነው።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ለትግራይ ክልል ህዝብ እርሻውን አርሶ፣ ሰብሉን አጭዶና ሰብስቦ በማስገበት ለዓመታት ህዝባዊ ወገንተኝነቱን በተግባር ያሳየ ባለውለታው እንደነበረም አስታውሰዋል።
"አሸባሪው ህወሓት ይህን አኩሪ ህዝባዊ ውለታ ክዶ ከጀርባ ሆኖ በመውጋት ታሪክ ይቅር የማይለው በሀገር ላይ ክህደት የፈጸመ የባንዳ ስብስብ ነው" ያሉት መቶ አለቃ ቻለው፣ "ሠራዊቱ የተፈጸመበት በደልና የከፈለው መስዋዕትነት ለዘላለም ሲዘከር መኖር አለበት" ብለዋል።
መቶ አለቃ ቻለው እንዳሉት ህወሓት ለዓመታት ህይወቱን በቀበሮ ጉድጓድ እያሳለፈ የህዝቡን ሰላም ጠብቆ መስዋዕትነት ለከፈለ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለአስከሬኑ እንኳ በክብር እንዳይቀበር ያደረገ ጨካኝ የሽብር ቡድን ነው።
ህወሃት ሀገር በሚመራበት ወቅትም የቀድሞ የኢትዮጵያን ሠራዊት በመበተን ለሠራዊቱም ሆን ለሀገር ምንም ደንታ እንደሌለው ማሳየቱንም መቶአለቃ ቻለው አስታውሰዋል።
"አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈጸመው የክህደትና ሀገር የማፍረስ ተግባር ቁጭት ስላሳደረብኝ ነው መከላከያ ሠራዊት ለመቀላቀል የወሰንኩት" ያለው ደግሞ በቅርቡ በክብር ከሰራዊቱ የተሸኘው ወታደር ሙልዬ ታፈረ ነው።
መከላከያ ሠራዊት ከምንም በላይ ለሀገሩ ዘብ የቆመ፣ ሀገሩን ለጠላት አሳልፎ የማይሰጥ ይልቁንም የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ከፍሎ ሀገርን የሚያጸና ጀግና መሆኑን ተናግሯል።
በመስዋዕትነት ለሀገር አለኝታ የሆነን ሠራዊት ተቀላቅሎ ሀገሩን በማገልገሉ ሁሌም ኩራትና ክብር እንደሚሰማውም ነው ወታደር ሙልዬ የገለጸው።
"የሽብር ቡድኑ ጥቅምት 24 ቀን በሠራዊቱ ላይ የፈጸመው የጭካኔ ተግባር ታሪክ አይረሳውም" ያለው ወታደር ሙልዬ፣ አሸባሪው ህወሓት የሀገር መከታ የሆነውን ሠራዊት ከጀርባው መውጋቱ ሳይበቃ ለአስክሬኑ ክብር ሳይሰጥ ለአሞራ ሲሳይ ማድረጉን አስታውሰዋል።
በወቅቱ መስዋዕት ለሆኑ የሠራዊቱ አባላት የሰማዕታት ክብር በመስጠት ሁሌም መዘከር እንደሚገባ ተናግሯል።
"በየዓመቱ ጥቅምት 24 መዘከሩ የሽብር ቡድኑን አረመኔነት እና የጭካኔ ተግባር ትውልዱ በሚገባ እንዲያውቀውና እንዲማርበት ያደርጋል" ያለው ደግሞ ሌላው በጎንደር ከተማዋ የሚገኘው ወታደር አሳየወርቁ ነው።
እንደ ወታደር አሳየ ገለጻ የሽብር ቡድኑ የሀገር ክህደት ወንጀል በታሪክ ተሰንዶ መቀመጥ አለበት።
"በአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች አስክሬኑ ተጎትቶ ጭካኔ የተፈጸመበት ሠራዊት አቅሙን አሰባስቦ መልሶ ለድል መብቃቱ ኢትዮጵያ ሁሌም በጀግኖቿ ተከብራ እንድምትጸና አንድ ማሳያ ነው" ብሏል።
ለሀገር መስዋዕትነት ሲከፍል ለኖረና ዛሬም በዱር በገደሉ ጠላትን እየተፋለመ ያለን ሠራዊት ጀግንነቱን ከፍ በማድረግና የሽብር ቡድኑን የጭካኔ ትግባር ለዓለም በማሳወቅ ዕለቱን መዘከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
"ዛሬም የትግራይን ህዝብ ከሽብር ቡድኑ የአፈና ስርአት ለማላቀቅ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እየከፈለ ያለው መስዋዕትነት በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው" ብሏል ወታደር ሲሳይ።
ሠራዊቱ ለትግራይ ህዝብ ገንዘቡንና ጉልበቱን ሳይሰስት ትምህርት ቤት፣ ጤና ተቋም እና ድልድይ ጭምር በመገንባት ከህዝብ አብራክ የወጣና የህዝብ ወገን መሆኑን በተግባር ሲያስመሰክር የቆየ መሆኑንም ተናግሯል።
መንግስት በሰሜን እዝ ላይ በአሸባሪው ህወሓት የተፈጸመውን የሀገር ክህደትና የጭካኔ ተግባር ለመዘከር በየዓመቱ ጥቅምት 24 እንዲታሰብ በወሰነው መሰረት ነገም እለቱ "መቼም አንረሳውም" በሚል መሪ ቃል እንደሚታወስ ይታወቃል።