ቀጥታ፡

አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ዘብ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት የማዳከም ተግባር ከመፈጸም ተቆጥቦ አያውቅም-የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት

ሀዋሳ፣ ጥቅምት 23/2015(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ዘብ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት የማዳከም ተግባር ከመፈጸም ተቆጥቦ አያውቅም ሲሉ ነዋሪነታቸውን በሀዋሳ ከተማ ያደረጉ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ገለጹ።

የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ህወሃት በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ክህደትና ጥቃት አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ለ28 ዓመታት ሀገራቸውን በኢትዮጵያ ሠራዊቱ ውስጥ ያገለገሉት ሻለቃ ጳውሎስ ጌታቸው "በሰራዊቱ ላይ በተፈጸመው ክህደትና ጥቃት የኢትዮጵያ ህዝብ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አንድ ላይ መቆሙን አሳይቷል" ብለዋል።

ሰራዊታችን ጥንትም በታሪክ የሚጠቀስ ብዙ ገድል አሉት ያሉት ሻለቃ ጳውሎስ ፤ አሁን ደግሞ የተሻለ ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑን ክህደት ከተፈጸመበት በኋላ ባገኘው ድል ማስመስከሩን ገልጸዋል።

ለአገሩ አንድነትና ሉዓላዊነት መጠበቅ እንዲሁም ለሰንደቅ ዓላማዋ ክብር ተስፋ ሳይቆርጥ ዋጋ የሚከፍል ሰራዊት እንደሆነ የሚታወቅ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

ሰራዊቱ ኢትዮጵያውያን የሚኮሩበት የቁርጥ ቀን ልጅ መሆኑን በሰላም ማስከበርና በልማት ተሳትፎ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ማስመስከሩንም ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪና በቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ለ22 ዓመታት ሀገራቸውን ያገለገሉት ሻምበል ሀብታሙ ገበየሁ አሸባሪው ህወሓት የነፍጥ ትግል ከጀመረበት ማግስት ጀምሮ ከትግራይ ህዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ባፈነገጠ መልኩ የመገንጠል አጀንዳ ይዞ የተነሳ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የመከፋፈል አጀንዳን ያነገበ እንደሆነ አንስተው በሰሜን እዝ ላይ ክህደት የፈጸመው አሸባሪው ህወሃት በስልጣን በነበረበት ጊዜም ሰራዊቱን የማዳከም ስራ ይሰራ እንደነበር አስታውሰዋል።

በብሔር በመከፋፈል ሰራዊቱን የማዳከም ተግባር በአሸባሪው ህወሃት ሲፈጸም የኖረ የአደባባይ ምስጢር መሆኑን አመልክተዋል።

ክህደትና ግፍ የተፈጸመበት የሰሜን ዕዝ ዳግም ራሱን አደራጅቶ አሸባሪው ህወሃትን ማሽመድመድ መቻሉን ገልጸው፤ ሰራዊቱ ህዝባዊነቱን ጠብቆ አጥፊዎችን መቅጣት የቻለ ታላቅ ሰራዊት መሆኑን እንዳስመሰከረ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም