ቀጥታ፡

ሰራዊቱ የተፈጸመበትን ግፍ ተቋቁሞ የሀገርን ሉዓላዊነት ያጸናበት መንገድ ኢትዮጵያውያንን ያኮራ ነው-የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

ጥቅምት 23/2015/ኢዜአ/ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በአሸባሪው ህወሃት የተፈጸመበትን የክህደት ግፍ ተቋቁሞ የሀገርን ሉአላዊነት ያጸናበት መንገድ መላው ኢትዮጵያውያንን ያኮራ መሆኑን የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡

አሸባሪው ህወሃት "እኔ ካልበላሁት ጭሬ ልበትነው" በሚል እኩይ መንፈስ አገር የመበተን አጀንዳ ይዞ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን እዝን ከጀርባ ማጥቃቱ ይታወሳል፡፡

ቡድኑ የሰራዊቱን መለዮ የለበሱና አብረውት የኖሩ ከዳተኛ አባላትን በማደራጀት ማንም ይፈጽመዋል ተብሎ በማይታሰብ ጭካኔ የአገር ሉዓላዊነት መከታ በሆነው መከላከያ ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ግፍ ፈፅሟል።

ከሃያ ዓመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ሆነው የአገር ሉዓላዊነትን ሲያስከብሩ፣ በትግራይ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ ሲገነቡ በኖሩ የሰሜን እዝ አባላት ላይ ያደረሰው የነውር ተግባር መቼውንም የማይረሳ ነው።

በሽብር ቡድኑ ከጀርባ የተወጋው የሀገር መከላከያ ሰራዊትም የሀገር ህውልናን የማስከበር ተልዕኮን ለመወጣት ራሱን በአጭር ጊዜ መልሶ በማደራጀት የአሸባሪው ህወሃትን እኩይ ተልዕኮ ያከሸፈ ድል ተቀዳጅቷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ተፈጸመው ድርጊት በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመ ክህደት መሆኑን ገልጸዋል።

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአሸባሪው ህወሃት የተከፈተበትን ጥቃት የቀለበሰበትና የሀገርን ሉዓላዊነት ያጸናበት መንገድ ኢትዮጵያውያንን  ያኮራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር መጋቤ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ቡድኑ በሰራዊቱ ላይ የፈጸመው ድርጊት አሳዛኝ ቢሆንም ሰራዊቱ ምላሽ የሰጠበት መንገድ ሁላችን የኮራንበት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር መብራቱ አለሙ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት ከራሱ አስተሳሰብ ውጭ የሆነ አካልን በሙሉ እየረሸነ የመጣ ቡድን  ነው ብለዋል።

በአንጻሩ የሰሜን ዕዝ ሰራዊት ከደሞዙ ቆርጦ ለህዝቡ አንቡላንስ የሚገዛና እናቶች በወሊድ ጊዜ እንዳይሞቱ ደሙን ሲለግስ የነበረ የህዝብ ሰራዊት መሆኑንም አንስተዋል።፡

ሆኖም መከላከያ ሰራዊቱ ለትግራይ ህዝብ አዝመራ እየሰበሰበ በነበረበት ወቅት በሽብር ቡድኑ ከጀርባ የተፈጸመበትን ጥቃት ከሰው ልጅ የማይጠበቅ እኩይነት ነው ይሉታል።

አመራሮቹ አክለውም ኢትዮጵያ ሁሌም በጀግኖች ልጆቿ እንደምትኮራ አንስተው፤ ጽኑ የሀገር ፍቅርና ዲሲፕሊን እንዳለው በተጨባጭ ያሳየው ሰራዊትም የሁላችንም መከታ መሆኑን አሳይቷል ይላሉ።

ሰራዊቱ የየትኛውም ፖለቲካዊ ኃይል ወገንተኛ እንዳልሆነና የኢትዮጵያ የሉዓላዊነቷ ጋሻ መሆኑን አረጋግጠናል ነው ያሉት፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችም የህዝብ መከታ የሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊትንና ኢትዮጵያን የሚዳፈር ማናቸውንም ኃይል እንደማይታገሱና ከሰራዊቱ ጎን በአንድነት እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም