አገር ያቆመ መስዋዕትነት

269

የአገር መከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ የውጭና የውስጥ ጥቃቶችን በጀግንነት በመመከትና ሉዓላዊነቷን በማስጠበቅ አኩሪ ታሪክ እንዳለው የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ።

በተሰጠው ግዳጅ ህዝብን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል እንዲሁም በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ተልዕኮዎች፣ በመልካም ስብዕናውና በጀግንነቱ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው ተቋም እንደሆነ ይመሰከርለታል።

እንደ አውሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ1950 ጀምሮ በተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ውስጥ በመሳተፍ የተመሰከረለት ታሪክ አቆይቷል።፡

የሰላም ማስከበር ተልዕኮውን በኮርያ የጀመረው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ላይቤሪያን ጨምሮ በአስራ አንድ የሰላም ማስከበር ዘመቻዎች ውስጥ በውጤታማነት ተሳትፏል፡፡

ለዓለም ሕዝቦችና ለቀጣናው ዋነኛ ጠላት የሆነውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በመመከት ቀጣናው ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ እንዲሆን በሱዳን ዳርፉርና በአብዬ ግዛት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ያሳየው ገድል የሚወሳ ነው።

ኢትዮጵያ በሺህ ዓመታት ታሪክ በልጆቿ ብርቱ ክንድ ነፃነቷንና አንድነቷን አስከብራ የኖረች ስትሆን  እንኳን ለአገር ውስጥ ባንዳዎች ሌሎች ሃያላንም ያልተንበረከከች መሆኗን ታሪክ ምስክር ነው።

ይህ ያልገባቸውና ከአገር በላይ የራሳቸው ጥቅም የበለጠባቸው ባንዳዎች ከኢትዮጵያ ጥንተ ጠላቶች ጋር በማበር አገሪቱን ለማፍረስ ከደደቢት በረሃ እስከ አራት ኪሎ ከ50 ዓመት በላይ የዘሩት ውጥን ሳይሰምርላቸው የቆዩ የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አመራሮችና አባላት መቀሌ ከመሸጉ ቆይቷል።

ጊዜው የቁርጥ ቀን ልጆች ኢትዮጵያን ለማሻገር አዲስ የለውጥ ጉዞ የቀየሱበትና ህዝቦቿን ከድህነት ለማውጣት በአዲስ መንፈስ የተነሳሱበት ነበር።

ይህ ያልተዋጠለት አፍራሽና ከፋፋይ ቡድን ግን ሴራውን ገፋበት።

የኢትዮጵያ የሉአላዊነት የመጨረሻ ምሽግ የሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ታሪክ የማይዘነጋው ጥቃት በመፈጸም ኢትዮጵያን ካደ።

እኔ ካልመራኋት ኢትዮጵያ ትፍረስ የሚለው ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝን በውድቅት ሌሊት በመጨፍጨፍ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጸመ።

የሰሜን ዕዝ ወታደሮችን ገድለው፤ ልብሳቸውን አውልቀው፤ አስከሬናቸውን አንድ ላይ ከምረው ሌሊቱን ሲጨፍሩ አደሩ።

በእናት ጡት ነካሽነት የተፈጸመ ታላቅ የክህደት ወንጀል የገደሉት የአገሩ ጠባቂና መኩሪያ የሆነውን የሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት ብቻ አይደለም ኢትዮጵያውያንን እንጂ።

የአሸባሪው ቡድን አመራሮች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል ድረሰ እንወርዳለን በማለት በየመድረኩ በማስተጋባት ክህደታቸውን እንደ ጀብድ ቆጠሩት።

የትግራይ ክልል ህዝብንና የአገሩን ዳርድንበር ሲጠብቅ የከረመው የህዝብ ልጅ ላይ የፈጸሙትን አጸያፊ ተግባር መብረቃዊ ጥቃት በማለት ተዘባበቱ።

ኢትዮጵያን ካላፈረሱ እረፍት እንደማይኖራቸውና የኢትዮጵያ መፍረስ የመጨረሻው የደስታቸው መለኪያና የእድለኝነታቸው መገለጫ አድርገው በመጥቀስ አገር ጠልነታቸውን በአደባባይ አወጡት።

መንግስት ለሰላም ሲል የወሰናቸውን ውሳኔዎች በመግፋት ሀዝብ እየጨፈጨፉ፣ ሴቶች እየደፈሩ፣ ንብረት እየዘረፉና እያወደሙ በድጋሚ ኢትዮጵያን መውጋታቸው አይዘነጋም።

ከኢትዮጵያ ጥንት ጠላቶች ጋር በማበር ከመቀሌ ደብረ ሲና ህዝብ እየገደሉ፣ የትምህርት ተቋማትና  የጤና ተቋማትን እያፈረሱና እየዘረፉ ሲሄዱና ይህንን ተግባራቸውንም እንደጀግንነት ሲገልጹ ሀፍረት አልነበራቸውም።

በህልም ዓለም ያሉ የአሸባሪው ቡድን አባላት እንዲያውም ጦርነቱ እንዳበቃና  ከማን ጋር እንደራደር የሚል አስተያየት በየመድረኩ ሲናገሩ የነበረበት ጊዜ እሩቅ አልነበረም።

ጀግናው መከላከያ ሰራዊት፣ የክልል የጸጥታ ሀይሎችና ደጀን የሆነው ህዝብ ግን ህልማቸውን ከንቱ አደረጉት።

ከአገር ክብር የሚበልጥ ነገር የለምና ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አህመድ ግንባር ድረስ በመዝመት ሰራዊቱን እየመሩ ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነትን ውጤታማ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በእርግጥም ኢትዮጵያ የማትሸነፍ መሆኗን ለወዳጅም ለጠላትም አሳይቷል።

በማይዛነፈው ጀግንነቱ ከራስ በላይ ለአገር በሆነው መርሁ ሞቶ ኢትዮጵያን እያዳነ ላለው መከላከያ ሰራዊት ክብር ይገባዋል።

ሰራዊቱ የሚከፍለው  አገር የማጽናት መስዋእትነት በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍ ያለ ስፍራ አለው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም