አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው ጥቃት አገራዊ አንድነትን እንደ አለት አጠንክሯል … የቀድሞ ሰራዊት አባላት

164

ሚዛን አማን፣ ጥቅምት 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) የአሸባሪው ህወሃት ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመው ጥቃት የኢትዮጵያውያንን በተለይም የሰራዊቱን አንድነት እንደ አለት ማጠናከሩን ነዋሪነታቸው በሚዛን አማን ከተማ የሆነ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ገለጹ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ህወሃት የህዝብ አለኝታና መከታ በሆነው የሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ክህደትና ጥቃት አስመልክቶ ኢዜአ ነዋሪነታቸው በሚዛን አማን ከተማ የሆኑ የቀድሞ ሰራዊት አባላትን አነጋግሯል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት አሥር አለቃ  ከተማ ዘለቀ  "ሰራዊቱ  የተገነባበት  ሥነ ልቦና፣ ጥንካሬና የህዝቡ ደጀንነት ኢትዮጵያ ለዘመናት ነጻነቷን አስከብራ እንድትቆይ አድርጓታል" ብለዋል።

ይህንን እውነት መቀበል ያልቻለው አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ  ላይ በፈጸመው  ግፍ ውርደትንና ሽንፈትን መከናነቡን ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት ይህንን የአገር ክህደት ድርጊቱን የፈጸመው ኢትዮጵያ ተበትና ለማየት ካለው ፍላጎት እንደመነጨ ገልጸው፤ የቡድኑ ክህደት ኢትዮጵያውያንን ይበልጥ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ማድረጉን አመልክተዋል።

"በአሸባሪው ህወሃት ክህደት ኢትዮጵያውያን  ከጫፍ ጫፍ  አንድነታቸው  ጎልቶ ታይቷል" ብለዋል።

ህወሃት መቼም ቢሆን ለኢትዮጵያ የማይበጅ አሸባሪ ቡድን መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ቡድኑን ለመዋጋት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

ሃምሳ አለቃ ብርሃኑ አሰፋ በበኩላቸው መቼም የማይረሳው የሰሜን ዕዝ ጥቃት መላውን ህዝብ እንደ አድዋ ትግል በእልህና በቁጭት ለዘመቻ ማነሳሳቱን ገልጸው፤ አሸባሪው ህወሓት የጥፋት በትሩን በመከላከያ ሰራዊት ላይ በመሰንዘር ሀገር የመበተን ተግባር ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ዘመኑ የሀገር ፍቅር የሌለው የጥፋት መልእክተኛ እንደነበር አስታውሰው፤ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጎን  በመሰለፍ  በሀገሪቱ ላይ  ተደጋጋሚ  ግፍና መከራ ለማድረስ ቢሞክርም ሊሳካለት አለመቻሉን አንስተዋል።

ቡድኑ በፈጸመው ክህደት በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ መደቆሱን አስታውሰው፤ ክህደቱ በየደረጃው  የሚገኘው  ህዝብ ለአገር  መከላከያ ያለውን  ፍቅርና  ደጀንነት አጠናክሮ እንዲያስቀጥል ማስቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም