አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው የክህደት ጥቃት ቡድኑ ጸረ ህዝብና ኢትዮጵያ ጠል መሆኑን በይፋ ያሳየበት ነው-ኮሎኔል ጌትነት አዳነ - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው የክህደት ጥቃት ቡድኑ ጸረ ህዝብና ኢትዮጵያ ጠል መሆኑን በይፋ ያሳየበት ነው-ኮሎኔል ጌትነት አዳነ
ጥቅምት 23/2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው የክህደት ጥቃት ቡድኑ ጸረ ህዝብና ኢትዮጵያ ጠል መሆኑን በይፋ ያሳየበት መሆኑን የመከላከያ የህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገለጹ።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከደጀኑ ህዝብ ጋር ሆኖ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት መቼውንም እንደማያስደፍር ተናግረዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ክህደት የፈጸመበት ጥቅምት 24 /2013 ዓ.ም ሁለተኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ቀኑን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች አስበውት እንደሚውሉ ገልጸው፣ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በኩል እና ሰራዊቱ ባለበት ቦታ ሁሉ በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች ታስቦ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም አሸባሪው ቡድን ሀገር የማፍረስ ተግባሩን ይፋ ያደረገበት ዕለት ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ ቡድኑ በፈጸመው የክህደት ተግባር ጸረ-ህዝብ እና ጸረ-ሀገር መሆኑን በተግባር ማስመስከሩን ጠቅሰዋል።
የሽብር ቡድኑ ቀድሞ ተዘጋጅቶ በተመሳሳይ ሰዓት የሰሜን ዕዝን ከጀርባ በመውጋት የፈጸመው ጥቃት ለአገራችን ቀርቶ ለዓለም እንግዳ የሆነ እኩይ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡
መከላከያ ሰራዊት ከራሱ በፊት ህዝብን አስቀድሞ ግዳጁን በብቃት የሚወጣ የህዝብ ልጅ ነው ያሉት ኮሎኔሉ፤ አሸባሪው ህወሓት ግን ታሪክ ይቅር የማይለው አስነዋሪ ተግባር ፈጽሞበታል ብለዋል፡፡
ሰራዊቱ በትግራይ ክልልም በፍጹም ወታደራዊ ዲሲፕሊን እና ህዝብ አክባሪነት ከ20 ዓመታት በላይ ተግባሩን ሲወጣ መቆየቱን ገልጸው፣ መለዮውን በለበሱና ወገኔ ብሎ ባመናቸው መከዳቱ እጅግ ያሳዝናል ነው ያሉት።
ድርጊቱም በኢትዮጵያውያን የታሪክ መዝገብ ውስጥ በመጥፎ ትውስታ የሚነሳ በመሆኑ ዕለቱን ስናስብ እንደዚህ ዓይነት ጥፋቶችን እንዳይደገሙ ለማስገንዘብ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በሰራቱ ላይ ጥቅምት 24 የደረሰውን ግፍ በማየት ከጎናችን ሆኖ አለኝታነቱን አስመስክሯል ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ ዛሬም ከጎናችን በመሆኑ ክብር ይሰማናል ብለዋል፡፡
ሰራዊቱም ከደጀኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሆኖ የሀገር ሉዓላዊነት ዘብነቱን በተግባር እያስመሰከረ መሆኑን በማንሳት ሰራዊቱ የትኛውንም ኃይል በብቃት መመከት የሚችልበት ቁመና ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን የመከላከያ ሰራዊቱን በግፍ የጨፈጨፈበት ጥቅምት 24 ሁለተኛ ዓመት በነገው ዕለት በመላ ሀገሪቱ "ጥቅምት 24ን መቼም አንረሳውም" በሚል መሪ ሀሳብ ይዘከራል።