የህወሀት የሽብር ቡድን የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎ ከመዝረፍ ባለፈ ሰራዊቱን በመውጋት አገር ለማፍረስ ሰርቷል - ኢዜአ አማርኛ
የህወሀት የሽብር ቡድን የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎ ከመዝረፍ ባለፈ ሰራዊቱን በመውጋት አገር ለማፍረስ ሰርቷል
አዳማ ጥቅምት 23/2015 /ኢዜአ/ የህወሀት የሽብር ቡድን ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎ ከመዝረፍ ባለፈ ሰራዊቱን በመካድ አገር ለማፍረስ መስራቱ ተገለጸ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሞ አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያን ሕዝብ ዳግም ያሳዘነበት ነው ይላሉ።
በዕለቱ አሸባሪው ሕወሃት የአገር ሉዓላዊነትን በመዳፈር የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት የማይረሳ ክስተት ነው ብለዋል።
የአገር ሽማግሌው አቶ ፈይሳ መገርሳ ''አሸባሪው ሕወሓት በሰራዊቱ ላይ የፈፀመው ግድያ የሁላችንንም ልብ የሰበረ ነበር'' ብለዋል።
መከላከያ ሠራዊቱ ለትግራይ ህዝብ ያልከፈለው ዋጋ እንደሌለ ያስታወሱት የአገር ሽማግሌው በጦርነት ጊዜ ጠላትን በመከላከል፣ በሰላሙ ጊዜ ደግሞ ከደመወዙ ጭምር በመቁረጥ በልማት ስራ ሲሳተፍ ነበር ብለዋል።
የአገር ሽማግሌው አቶ ፈይሳ የሽብር ቡድኑ ''እኛ ካልገዛንህ፣ እኛ ካላስተዳደርንህ አገር ትጠፋለች ብሎ የፈፀመው ከህደት መሆኑን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይገነዘባል'' ሲሉ ይገልጹታል።
ቡድኑ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ከፋፍሎ ዘረፋ ሲፈጽምበት ከቆየ በሗላ ሰራዊቱን መካዱና አገር መድፈሩ ታሪክ የማይረሳው ክስተትም ነው ብለዋል።
በአንድነቱና በሉዓላዊነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በአንድነት ተነስቶ አሸባሪውን መክቶ ዳግም አገሩን አስከብሯል ብለዋል የአገር ሽማግሌው።
''የአደዋ ድል የተገኘው በአንድነት ነው፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተነስተው የትኛውንም ጠላት እንደሚመክቱ መልዕክት የተላለፈበት ወቅት ነው '' ብለዋል።
ሀጅ ሁሴን ሀሞ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ የፈጸመው ጥቃት ዓላማው አገር የማፍረስ ጥቃት ነው፤ በወቅቱ ኢትዮጵያውያንና የዓለምን ህዝብ ጭምር ያሳዘነ ተግባር መፈፀሙን ነው ያነሱት።
ሕዝቡ በዘርና በኃይማኖት ሳይከፋፈል እንደ ጥንቱ ሁሉ በአንድነት በመቆም የጠላት ተልዕኮ እንዲከሽፍ አድርጓል ብለዋል።
አባገዳ መርጋ ለገሰም እንዲሁ ''ጥቅምት 24ትን ስናስብ አሸባሪው ሕወሓት የሀገር ሉዓላዊነትን በመዳፈር የመከላከያ ሠራዊት ላይ የፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት እንዳይደገም አንድነታችንን በማጠናከር ነው'' ብለዋል።
ወደ ፊትም ሕዝቡ ከአገር መከላከያ ጎን ሆኖ የአገሩን ሉዓላዊትና የሕዝቡን አንድነት ለመጠበቅ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ መደገፍ እንዳለበትም ነው የገለጹት።