ቀጥታ፡

አሸባሪው የህወሀት ቡድን በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ክህደት የፈጸመበት ቀን በልዩ ሁኔታ ታስቦ ይውላል

ጥቅምት 23/20215 /ኢዜአ/ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ክህደት የፈጸመበት ጥቅምት 24 በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በኩል በልዩ ሁኔታ ታስቦ እንደሚውል የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ የጥቅምት 24 መታሰቢያን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም ክህደት የማይሰለቸው አሸባሪ ቡድን አገር የማፍረስ ዓላማን አንግቦ ሰራዊቱ ላይ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ገልጸዋል።

ቡድኑ በፈጸመው የክህደት ተግባርም ጸረ ህዝብ እና ጸረ አገር መሆኑን በተግባር አስመስክሯል ብለዋል።

የዕለቱ 2ኛ ዓመት መታሰቢያም በነገው ዕለት በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በኩል እና ሰራዊቱ ባለበት ቦታ ሁሉ ታስቦ እንደሚውል ተናግረዋል።

የበዓሉ መከበርም እንዲህ ያለ የጥፋት ተግባር ዳግም እንዳይታሰብ ለማስገንዘብም ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ቂምና ጥላቻን ለመግለጽ ሳይሆን ይህ የክህደት ተግባር ዳግም እንዳይፈጸም ጭምር ለማስተማር እና ለማስገንዘብ ነውም ብለዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን የመከላከያ ሰራዊቱን በግፍ የጨፈጨፈበት ጥቅምት 24 ሁለተኛ ዓመት በነገው ዕለት ይታሰባል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም