አዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ሶርሲንግ የጨርቃ ጨርቅ ንግድ ትርኢት ላይ ከ30 ሀገራት የተውጣጡ አምራቾች ይሳተፋሉ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ሶርሲንግ የጨርቃ ጨርቅ ንግድ ትርኢት ላይ ከ30 ሀገራት የተውጣጡ አምራቾች ይሳተፋሉ
ጥቅምት 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በሚካሄደው የአፍሪካ ሶርሲንግ ዓለም አቀፍ የጨርቃጨርቅ ንግድ ትርኢት ላይ ከ30 ሀገራት የተውጣጡ 200 አምራቾች እንደሚሳተፉ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ገለጸ።
8ኛው የአፍሪካ ሶርሲንግ ዓለም አቀፍ መድረክና የፋሽን ሳምንት ከጥቅምት 25 እስከ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል።
ሁነቱን አስመልክተው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በሰጡት መግለጫ፤ በንግድና ትርኢቱ ተሳታፊዎች መካከል 39 የሚሆኑት የኢትዮጵያ አምራቾች መሆናቸውን ገልጸዋል።
መርሐ-ግብሩ አምራቾች የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት፣ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትናግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደህ አይነት እድሎች የጨርቃጨርቅ አምራቾችን ለማጠናከርና አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን የንግድ ድርሻና ደረጃ ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።
ከንግድ ትርኢቱ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ እንደሚካሄድ ሚኒስትር ዴኤታው ጨምረው ገልጸዋል።
የመርሐ-ግብሩ ተባባሪ አዘጋጅ የሆነው የመሴ ፍራክፈርት ድርጅት ስራ አስኪያጅ እስክንድር ነጋሲ አፍሪካ ሶርሲንግ የፋሽን ሳምንት የአፍሪካን አምራቾች ለማቅራረብ የጎላ ሚና እንዳለው ተናገረዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የጨርቃጨርቅ አምራቾች ከሌሎች ሀገራት ልምድ የሚቀስሙበት ጥሩ አጋጣሚ መሆኑን ጠቅሰው የሀገሪቱን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በባዛሩ ከ6 ሺህ በላይ የዘርፉ ነጋዴዎች፣ ሸማቾችና ግብዓት አቅራቢዎች እንደሚሳተፉም ስራ አስፈሚው ገልጸዋል።
ስምንተኛው የአፍሪካ ሶርሲንግ እና የፋሽን ሳምንትን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና መሴ ፍራንክፈርት በትብብር አዘጋጅተውታል።