ቀጥታ፡

የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴርና ፓውር ፎር ኦል የቴክኒክ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

ጥቅምት 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ከፓውር ፎር ኦል ጋር ከ2022 እስከ 2025 ለሶስት ዓመታት የሚቆይ የቴክኒክ እና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ እና የፓዎር ፎር ኦል ዋና ስራ አስፈጻሚ ክሪስቲና ኪየርካ ናቸው።

በዚህም ፓዎር ፎር ኦል የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ማድረግ፣ ግብርናን የመደገፍ የቴክኒክና የአቅም ግንባታ ስልጠና ለባለድርሻ አካላት የመስጠት ስራዎችን እንደሚሰራ ተገልጿል።

የመስኖ  ልማት ፕሮጀክቶች የታዳሽ ኃይልን ተጠቅመው ምርታማነትን ለመጨመር የሚያስችላቸውን ስራም በቅንጅት እንደሚሰራም ተጠቁሟል።

የፓዎር ፎር ኦል ድጋፍ የኢትዮጵያን ግብርና በታዳሽ ኃይል ለመደገፍ እና የመስኖ ስራን የበለጠ ለማሻሻል እንደሚያስችል የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

በተለይ ከዋናው የሃይል መስመር ውጭ ያሉ የመስኖ መሰረተ ልማቶች የታዳሽ ኃይልን ተጠቅመው ውሃን ወደ ማሳ በማድረስ ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ በመጠቆም።

የፓዎር ፎር ኦል ዋና ስራ አስፈጻሚ ክሪስቲና ኪየርካ በስምምነቱ መሰረት የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በተለይም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን በታዳሽ ኃይል እንደግፋለን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም