ቀጥታ፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ አስፈላጊውን እናደርጋለን

አምቦ ፣ጥቅምት 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) የምዕራብ ሸዋ ዞን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ገለጸ።

በሰሜን ሸዋ ዞን የቆየው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ዛሬ በምዕራብ ሸዋ ዞን ጉደር ከተማ ሲገባ በህዝቡ አቀባበል ተደርጎለታል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የአገሪቷ ልማት ምሰሶ የሆነው የግድቡ ግንባታ ዳር ለማድረስ በዞኑ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት ከሚያከናውናቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ አንዱ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ ሀገር ለማስረከብ የግድቡ ግንባታ ስኬት ወሳኝ በመሆኑ የዞኑ ሕዝብ እንደከዚህ በፊቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ በዞኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ግዢና በስጦታ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

የቶኬ ኩታዬ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሃብታሙ ለታ በበኩላቸው ለግድቡ ግንባታ ማስፈጸሚያ 100 ሺህ ብር በቦንድ ግዢ እና የ50 ሺህ ብር ስጦታ መበርከቱን ገልጸው ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡

በአቀባበል ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ተወካዮችም ተገኝተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም