ቀጥታ፡

ተቋማቱ የአሊባባ ቢዝነስ ግሩፕ ዌል ክላውድ የኢ-ኮሜርስ አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለማስጀመር የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

ጥቅምት 22/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት፣ የአሊባባ ቢዝነስ ግሩፕ እና ከሃሊ የስትራቴጂክ አማካሪ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የሶስትዮሽ መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱም የኢትዮጵያን የዲጅታል ኢኮኖሚ እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ለማህበረሰቡ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማድረስ እንደሚረዳ ተገልጿል።

የሶስትዮሽ ስምምነቱም ግዙፉን የቻይና ዓለም አቀፍ የኦንላይን ኢ-ኮሜርስ መገበያያ ስርዓትን በዌል ክላውድ የአሊባባ ቢዝነስ አማካኝነት በኢትዮጵያ ለማስጀመር እንደሚያስችል ተጠቁሟል።

በስምምነቱ መሰረት የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለዌል ክላውድ አሊባባ ቢዝነስ ግሩፕ የስራ ምህዳርን ምቹ ለማድረግ የሚያስችል የመረጃ ማዕከል (ዳታ ሴንተር) ያቀርባል ተብሏል።

ከሃሊ የስትራቴጂክ አማካሪ አገልግሎት ደግሞ የዌል ክላውድ ስራዎችን በኢትዮጵያ ለመተግበር ምቹ ምህዳርን ለመፍጠር፣ የክፍያ መንገዶችን ለማመቻቸት፣ የሶስትዮሽ ስምምነቱን ለማስተዋወቅ ይሰራል።

የባንክ ስርዓቱን ለማዘመን የሚያግዙ የፋይናንስ ዘርፍ እና የክፍያ መዋዕለ ነዋይን ፈሰስ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ለመስራት ከባንኮች ጋር ድርድር ማድረጉ ተመላክቷል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና፣ በአሊባባ ቢዝነስ ግሩፕ የዌል ክላውድ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የግዥ ዳይሬክተሩ ዚይ ዪህ እና የከሃሊ የስትራቴጂክ አማካሪ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤርሚያስ አመልጋ ተፈራርመውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም