ቀጥታ፡

አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት የአሸባሪው ህወሃትን ወንጀሎች የማያወግዙት ቡድኑ በቀጣናው ያላቸውን ፍላጎት ስለሚያስፈጽም ነው

ጥቅምት 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) "አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት አሸባሪው ህወሃት በቀጣናው የፍላጎታቸው ማሳኪያ በመሆኑ ኢትዮጵያ ላይ የሚፈጽማቸውን የጭፍጨፋና የወረራ ወንጀሎች ለማውገዝ ፍላጎት የላቸውም" ሲሉ በኳታር የኢትዮጵያ አምባሳደር ፈይሰል አሊዪ ተናገሩ።

አምባሳደር ፈይሰል ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሸባሪው ህወሃት መቼም ቢሆን ለኢትዮጵያ ጥቅምና ፍላጎት ታማኝና ተገዥ ሆኖ አያውቅም።    

ኢትዮጵያ ወደ ጦርነት ተገድዳ የገባችው የሽብር ቡድኑ ሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ጥቃት በመክፈቱ መሆኑ ገሃድ ቢሆንም ምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃንና አንዳንድ አገራት ግን እውነታውን ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸው ትዝብትን ያጭራል ብለዋል።     

መንግስት የሽብር ቡድኑ ጠብ አጫሪነቱን እንዲያቆም ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ቢያቀርብም የሽብር ቡድኑና ጋላቢዎቹ ጉዳዩን በቸልታ ማለፋቸውን በመጥቀስ።  

ከዚህም በላይ የትግራይ ክልል አርሶ አደር የግብርና ስራውን እንዲያከናውንና ለሰብዓዊ ዓላማ በተከታታይ የተኩስ አቁም ማድረጉንም ምዕራባውያኑ እንደ በጎ ተግባር አልቆጠሩትም ነው ያሉት።

አሸባሪው ህወሃት በእብሪት እና ዛቻ ሁለተኛውን ዙር ጦርነት በመክፈት በአጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመበት ወቅት አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት የሽብር ቡድኑን ወንጀል ለማውገዝ አልሞከሩም ነው ያሉት።

መንግሥት ለትግራይ ህዝብ ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ብዙ ጥረት ማድረጉን የጠቀሱት አምባሳደር ፈይሰል፤ የሽብር ቡድኑ ግን እርዳታውን ለታጣቂዎቹ ከማዋሉ ባለፈ ራሱን በማደራጀት ሦስተኛ ዙር ጦርነት መክፈቱን አስታውሰዋል።      

ቡድኑ ንጹሃንን በመረሸን፣ ህጻናትና ሴቶችን ለስቃይ ሲዳርግ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃንና ምዕራባውያን እውነታውን መቀበል አለመፈለጋቸው አሳዛኝ መሆኑንም ተናግረዋል።  

ለዚህም ዋነኛው ምክንያት አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያና በአጠቃላይ በቀጣናው ላይ ጫና ለሚያደርጉ አንዳንድ ኃይሎች ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም ስለሚሰራ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በሀገሩ ላይ የተቃጡ የጣልቃ ገብነት ሙከራዎችንና የሽብር ቡድኑ እኩይ ተግባራት በነቂስ ወደ አደባባይ ወጥቶ ማውገዙን ያነሱት አምባሳደር ፈይሰል፤ በዚህም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለድርድር እንደማይቀርብ አቋሙን አሳይቷል ነው ያሉት።

የትኛውም የውጭ ኃይልና የውስጥ ባንዳ ተባብሮ ኢትዮጵያን እንዲያውክ እንደማይፈቅድ ህዝቡ ደጋግሞ አሳይቷል ይህም ትልቅ ክብርና ዋጋ የሚሰጠው ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለቀጣናው ሠላም ሁሌም የምትተጋ አገር መሆኗን ከግምት በማስገባት ሁሉም ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንደሚገባውም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም