ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብ ከአሸባሪው ህወሓት ጭቆና ነጻ እንዲወጣ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደግፋለን--የክልሉ ተዋላጆች

ኮምቦልቻ ጥቅምት 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) "የትግራይ ክልል ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት እየደረሰበት ካለው ግፍና ጭቆና ለማላቀቅ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት እንደግፋለን" ሲሉ በኮምቦልቻ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ገለጹ።

የትግራይ ክልል ተወላጆች አሸባሪውን ህወሓትና በአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት ኢትዮጵያ ላይ እየተደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት የሚቃወም ሰልፍ በኮምቦልቻ ከተማ አካሂደዋል።

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አርዓያ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አሸባሪው ህወሓት የክልሉን ህዝብ አፍኖ በመያዝ አሰቃቂ ግፍና በደል እየፈጸመበት ይገኛል።

የሽብር ቡድኑ ሕፃናትን አስገድዶ ለጦርነት ከማሰለፍ ባለፈ ወላጆች ያለጧሪና ቀባሪ እንዲቀሩ ማድርጉንም አስታውሰዋል።

"ለህዝብ የመጣን የእርዳታ እህል ሰርቆ ለተዋጊዎች በመስጠት ህዝቡ የእለት እርዳታ እንኳ ሳያገኝ ለተለያዩ ችግሮች እንዲጋለጥ አድርጓል" ሲሉም ገልጸዋል።

"የአሸባሪው ህወሓትን የጭካኔ ተግባር በማጋለጥና ከመንግስት ጎን በመቆም የትግራይ ህዝብ እየደረሰበት ካለው ግፍና መከራ ነጻ እንዲወጣ የድርሻችንን ለመወጣት በሰልፉ ላይ ተሳትፈናል" ብለዋል።

አቶ አርአያ እንደገለጹት፤ "መንግስት በትግራይ ሰብዓዊ እርዳታን ለማድረስና ህዝቡ የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኝ ዳግም የጀመረው እንቅስቃሴ እንደሚደግፉትና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን" ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመደገፍና ከጎኑ በመቆም የሽብር ቡድኑን ቀብር ማፋጠን እንዳለበትም አመልክተዋል።

ሌላው የሰልፉ ተሳታፊ አቶ ተመስገን በርሄ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ በማለም በተደጋጋሚ ባካሄደው ጦርነት በህዝብ ላይ ጭካኔ የተሞላበት አስነዋሪ ግፍና መከራ መፈጸሙን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑን ግፍና ድብቅ ሴራ በማጋለጥ ድርጊቱን ለማውገዝ ሰልፍ መውጣታቸውን ገልጸው፣  መንግስት የጀመረውን የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እንዲያጠናክር የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የሀገር ኩራት የሆነውን መከላከያ ሠራዊት "ሊያጠፋህ መጣ" በማለት በሀሰት ሥሙን ለማጠልሸት የሚነዛን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ሁሉም አውቆ እውነታውን ማጋለጥ ይገባል ሲሉም አክለዋል።

የክልሉ ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት የተለያየ በደልና ግፍ ሲፈጸምበት መቆየቱን የገለጹት አቶ ተመስገን፤ ህዝቡ ከአሸባሪው ቡድን ጭቆና ነጻ እንዲወጣ የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ አረጋግጥዋል። 

"የትግራይ ክልል ህዝብ ነጻ ወጥቶ ከሌላው ኢትዮጵያዊ እህትና ወንድሞቹ ጋር በአንድነት እንዳይኖር የሚሠሩ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት ያልተገባ ጣልቃ ገብነትን እንቃወማለን" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ሰላም ገብረጊዮርጊስ ናቸው።

"አሸባሪው ህወሓት ከእናቶች ጉያ ልጃቸውን እየነጠቀ ታሪክ የማይረሳው ግፍ እየፈጸመ በመሆኑ መንግስት ሽብር ቡድኑን በማጥፋት ለእነዚህ እናቶችም ሊደርስላቸው ይገባል" ብለዋል።

የአሸባሪው ህወሓት ዕድሜ እንዲራዘም በኢትዮጵያ ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩ የውጭ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡም ወይዘሮ ሰላም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የትግራይ ክልል ህዝብ በአሸባሪው ህወሓት እየደረሰበት ካለው ጭቆናና ግፍ ለማውጣት እየከፈለ ያለውን መስዋዕትነት እንደሚደግፉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም