አሸባሪው ሕወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነትን ለማፍረስ ያለመ ነበር - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ሕወሃት በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነትን ለማፍረስ ያለመ ነበር
ጥቅምት 22/2015(ኢዜአ) አሸባሪው ሕወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ የግዛት አንድነት አፍርሶ ለውጭ ታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ ለመስጠት ያለመ እንደነበር ተገለጸ።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ አርበኝነት ታፍራና ነጻነቷን አስከብራ ብትቆይም በየዘመኑ ባንዳና ጠላቶች ፈትነዋታል ይላሉ።
አሸባሪው ሕወሃት የጠላቶችን አጀንዳ ለማስፈጸም እንዲሁም ለራሱ ስልጣንና ጥቅም ህዝብን በተለያዩ ማንነቶች እርስ በርስ ለመከፋፈል ያልፈነቀለው ድንጋይ እንዳልነበር ገልጸዋል።
ቡድኑ ከማዕከላዊ መንበረ ስልጣኑ በህዝብ ግፊት ከተወገደ በኋላም ኢትዮጵያን ለጠላት አሳልፎ የመስጠት ባንዳነት ነውሩን እንደቀጠለበት አውስተዋል።
አሸባሪው ቡድን ከ20 ዓመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የሀገር ሉዓላዊነትን ሲያስከብርና የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅና ክልሉን ሲያለማ የቆየው የሰሜን ዕዝ ሰራዊት ላይ ከፈጸመው የክህደትና የግፍ ጭፍጨፋ ጀርባ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለጠላት ማጋለጥና ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ነበረው ብለዋል።
የሰሜን ዕዝ ጭፍጨፋ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ያለፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ የጀመረቻቸውን የልማት ውጥኖች ለማሰናከል በታሪካዊ ጠላቶች አይዞህ ባይነት የተፈጸመ ድርጊት ነበር ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የጥቁሮች የነጻነት ፋና መሆኗን ያልወደዱ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገሪቱን ለማዳከምና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ለማምጣት አሸባሪውን ሕወሃትና ባንዳዎችን በትሮይ ፈረስነት ተጠቅመዋል ነው የሚሉት።
በዚህም በሰሜን ዕዝ የተፈጸመው ጥቃት በዓለም ከተፈጸሙ አሰቃቂና ዘግናኝ ድርጊቶች የከፋ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት ከ30 ዓመታት በላይ በታንከኛ ክፍል ያገለገሉት ብርጋዴር ጀኔራል ዋሲሁን ንጋቱ የጥቅምት 24ቱ ሰሜን ዕዝ ጥቃት ዛሬም ለሰሚው ግራ፣ በታሪክም መጥፎ ትውስታ ነው ይሉታል።
አሸባሪው ሕወሃት በደርግ ዘመንም ሆነ በኋላ በኢትዮጵያና በህዝቧ ላይ የፈጸመው ግፍና በደል በየትኛውም መንገድ የማይሻር ጠባሳ መሆኑን ገልጸዋል።
ቡድኑ የኢትዮጵያ የሉዓላዊነት ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ከጀርባ በመውጋት የፈጸመው ጭፍጨፋ ግቡ የኢትዮጵያን ሉአላዊ የግዛት አንድነት በመጣስ ሀገርን በታትኖ ለጠላት ለመስጠት መሆኑን አንስተዋል።
አስተያየት ሰጭዎቹ በሰሜን ዕዝ ጭፍጨፋ ለተሰው የኢትዮጵያ ወታደሮች መታሰቢያ ማቆም፣ ለሰራዊት ቤተሰቦችም ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ከመንግስትና ከህዝቡ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ጠላትና ባንዳ ቢፈራረቁባትም በጀግኖች ልጆቿ መስዕዋትነት ፀንታ እንደምትቀጥልም ነው የተናገሩት።
ለሀገሩ ክብርና ሉዓላዊነት የህይወት መስዕዋትነት ለሚከፍለው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊትም ዕውቅና መስጠት መጀመሩ ሌሎች ጀግኖችን ለማፍራት ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም አንስተዋል።