''ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ከመሆን የሚለየን የለም''-የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
''ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ከመሆን የሚለየን የለም''-የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ነዋሪዎች
ጭሮ ጥቅምት 22 ቀን 2015 (ኢዜአ) ''ከመከላከያ ሰራዊታችን ጎን ከመሆን የሚለየን የለም'' ሲሉ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
አሸባሪው ሕወሓት የአገር ክህደቱን የጀመረው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝን በማጥቃት ነበር።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ራሱን አደራጅቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ደጀን አድርጎ ጥቃቱን መከተው፣ አገርንም አዳነ።
ከሃዲውና አሸባሪው ቡድንም ያሰበው አገር የመበተንና የማፍረስ ሕልም ሳይሳካለት ቀረ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ነዋሪዎች፤ ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ የተጠበቀችውና የተከበረችው በመከላከያ ሰራዊት ነው ይላሉ።
ለዚህም ነው ነዋሪዎቹ የአገር መከታ ከሆነው ሰራዊት ጎን ሆነው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ሲወጡ የቆዩት።
የሀገር ሽማግሌው አቶ አወል አልዪ፤ የሀረርጌ ህዝብ በአገሩ ጉዳይ ሁሌም በአንድነት የሚቆምና የሚተባበር ሕዝብ ነው ይላሉ።
አሸባሪው ሕወሓት የአገር ክህደት ሲፈጽምም ሕዝቡ ከመንግስትና ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ቆሞ በሚችለው ሁሉ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
‘’የመከላከያችን ጉዳይ የሀገራችን ጉዳይ ነው፤ የአገራችን ጉዳይ ደግሞ የማንነታችን ጉዳይ ነው ብለን ከሰራዊቱ ጎን ቆመናል’’ ነው ያሉት።
እሳቸውም ከዞኑ ነዋሪዎች ጋር በመሆን ከሰራዊቱ ጎን መቆማቸውን ለማሳየት ከሰላማዊ ሰልፍ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ወደ ፊትም በመከላከያ ሰራዊትና በአገር ላይ የመጣን አደጋ ለመመከት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አባገዳ ኢብራሂም መሀመድ የዞኑ አባገዳዎች ሕብረት ሕዝቡ የአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን እንዲቆም ሕዝቡን ሲያነቃቃ መቆየቱን ይናገራሉ።
''መከላከያ ሰራዊቱን መደገፍ ከሁሉም ጉዳዮች የሚቀድም በመሆኑ በድጋፉ ላይ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆንና ሀገሩን እንዲወድ፤ ወደ ራሱ እንዲመለከት የማድረግ ስራ እየሰራን ነው'' ብለዋል።
በዞኑ የጭሮ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ወዚራ አህመድ ‘’ለሀገራችን ክብር ለቆመው መከላከያ ሰራዊታችን የምንሰስተው ነገር የለም፤ ሁሌም ከጎኑ እንደምንቆም አረጋግጣለሁ’’ ብለዋል።
‘’ራሱን ሰውቶ አገራችንን ከመበታተን ለሚጠብቀው መከላከያችን እያደረግን ያለነው ድጋፍ ሲያንስበት እንጂ አይበዛም፤ ይቀጥላልም’’ ሲሉ አክለዋል፡፡
አቶ መሀመድ ኡስማንም የሀረርጌ ህዝብ ኢትዮጵያ የትኛውንም ጫና እንድትቋቋም የሚጠበቅበትን የሚወጣ ሕዝብ ነው ብለዋል።
የዞኑ ወጣቶችም ለአገር ሉዓላዊነት ሲባል የሚከፈለውን መሰዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ይናገራሉ።
ወጣት ኢብሮ አብደላ ኢትዮጵያ ጸንታ የቆመችው ቀደምት አባቶች በከፈሉት መሰዋዕትነት በመሆኑ አሁንም ኢትዮጵያን ለማስቀጠል የሚከፈለውን ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነ ተናግሯል።
አስተያየት ሰጪዎቹ አሸባሪው ሕወሓት የሰሜን ዕዝን በማጥቃት አገር ለማፍረስ የሞከረው ድርጊት መቼም ከኢትዮጵያውያን ልብ የማይጥፋ ክስተት እንደሆነም ነው ያነሱት።
የምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቶፊቅ አህመድ እንደገለፁት የዞኑ ሕዝብ የአገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ሂደት በአራት ዙር የተለያዩ ድጋፎችን አድርጓል ብለዋል።
በገንዘብ ደረጃ 87 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር 80 የእርድ ከብቶች እንዲሁም ሶስት የጭነት መኪና የተለያዩ ደረቅ ስንቅ ከዞኑ ሕዝቦች በማሰባሰብ ለአገር መከላከያ ሰራዊት ተሰጥቷል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ምን ጊዜም ቢሆን አጥር ሆኖ ለሚጠብቀው መከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚችል በተግባር አረጋግጧልም ብለዋል ኃላፊው።