ቀጥታ፡

ሚሲዮኖች ወቅቱን የሚመጥን የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው

ጥቅምት 22/2015 (ኢዜአ) ሚሲዮኖች ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም እየጨመረ ከሚመጣው ጫና ጋር የሚመጣጠን የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባቸው ተመላከተ።

በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስተባባሪነት በተዘጋጀና ባለፉት ዘጠኝ ሳምንታት በሚሲዮኖች የተከናወኑ የዳያስፖራ የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ንቅናቄዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በውይይቱ ላይ እንዳሉት ሚሲዮኖች የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን በማስተባበርና መደበኛ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።

መንግስት ስራዎቹን ለመደገፍ አስፈላጊ የሆኑ የመረጃ አቅርቦትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ሚሲዮኖች ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም የጀመሩትን እንቅስቃሴ በጥራትና በይዘት በማሳደግ እየጨመረ ከሚመጣው ጫና ጋር የሚመጣጠን የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ መድረኩ በሚሲዮኖች ተሞክሮ እንዲለዋወጡና የተጀመሩ የዳያስፖራ ፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ንቅናቄ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የዲፕሎማሲ ዕቅድ ስራው በማዕከል ክትትልና ድጋፍ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስታውሰው፤መድረኩ ተጨማሪ ሃላፊነቶች የሚወሰዱበትና ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች የሚመላከቱበት ይሆናል ብለዋል።

አምባሳደሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ በመደበኛውም ሆነ መደበኛ ባልሆነው የሚዲያ ዘርፍ እያደረጉ ያለው ተሳትፎ እያደገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ተሳትፎው ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ያሉት ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ናቸው ።

ሚሲዮኖቹ እያደረጉ ያለውን ጥረት ለመደገፍ የአቅም ግንባታ ስራ ለማከናወን መታቀዱንም ገልጸዋል።

በአምባሳደሮችና ሚሲዮኖች እየተከናወኑ ባሉ የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ ስራዎች አንጻር ትኩረት ያሻቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተው ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።

አምባሳደሮችና የሚሲዮን መሪዎችም በየሚወክሉት ሀገር ያለውን የዳያስፖራና ሌሎች የፐብሊክና ዲጂታል ዲፕሎማሲ አቅሞችን በመጠቀም የሀገርን ጥቅም ለማስጠበቅ ስራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም