ቀጥታ፡

የመጀመሪያው የኢሬቻ የሠላም ሽልማት ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ መስከረም 15/2011 የመጀመሪያው የኢሬቻ የሠላም ሽልማት ሊካሄድ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከል አስታወቀ፡፡ የሽልማቱ ሥነ-ሥርዓት በመጪው አርብ በማዕከሉ ቅጥር ግቢ ይከናወናል፡፡ ማዕከሉ ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር በዓለም ዓቀፍ ቅርስነት የተመዘገበውንና የአንድነት፣ የሠላም፣ የእርቅና የደስታ መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ለማክበር ዝግጅት አጠናቋል፡፡ በማዕከሉ የሕዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰብለ አበበ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት የኢሬቻ የሠላም ሽልማት የክልሉን ባህል ለመጠበቅ፣ ለማስተዋወቅ ብሎም በባህሉ የሚኮራ ዜጋ ለመፍጠር ሚናው የጎላ ነው፡፡ በአገሪቱ ሠላም ለማምጣት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ባለውለታዎች የመጀመሪያውን የኢሬቻ የሠላም ሽልማት ያገኛሉ ብለዋል፡፡ የሽልማቱ ዋና ዓላማ በመቻቻል በመከባበር በህዝብ መካከል ሠላም እንዲፈጠር፣ የነበረው ባህል እሴቱን ሳይለቅ ሳይሸረሸር ተጠብቆ እንዲቀጥል ላደረጉ ወገኖች ለማመስገን ጭምር መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ በዕለቱም ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ይካሄዳል፣ በዓሉ በአውደ ርዕይና በሙዚቃ ይከበራልም ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፡፡ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ አባገዳዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የክልልና የዞን አመራሮች፣ ምሁራንና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይሳተፋሉ፡፡ ማዕከሉ የህዝብ በዓላት ይዘታቸውን ሳይለቁ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡ በመጪው እሁድ መስከረም 20 ቀን 2011 ዓም በቢሾፍቱ ከተማ የሚከበረው ኢሬቻ በኦሮሞ ባህል የሚከናወን የምሥጋና በዓል ነው፡፡                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም