አየር መንገዱ በ50 ሚሊዮን ዶላር እያስገነባ ያለው ዘመናዊ የኢ-ኮሜርስ የጭነት አገልግሎት ማዕከል በቅርቡ ስራ ይጀምራል

40

ጥቅምት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ50 ሚሊዮን ዶላር እያስገነባ ያለው ዘመናዊ የኢ-ኮሜርስ የጭነት አገልግሎት ማዕከል በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር አስታወቀ።

በአሁኑ ወቅት በዓለም የኢ-ኮሜርስ ንግድ እየተስፋፋ መሆኑን ተከትሎ አየር መንገዱ ተወዳዳሪነቱን ለማስቀጠል የካርጎ አገልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የቦርድ ሰብሳቢ ግርማ ዋቄ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ አየር መንገዱ በካርጎ አገልግሎት ከአፍሪካ ትልቁና በዓለም ተወዳዳሪነቱን ለማስጠበቅ ዘመናዊ አሰራርን ይከተላል።

በዓለም  ላይ የዲጂታል ግብይት እያደገ በመምጣቱ የመደበኛው ካርጎ አገልግሎት እየቀነሰ በአንጻሩ የኢ-ኮሜርስ የካርጎ አገልግሎት እየሰፋ መምጣቱን አንስተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሎጅስቲክስ ዘርፉ ይህን አሰራር መከተል የግድ ይላቸዋል ብለዋል።

አዲሱን የካርጎ አገልግሎት ማዕከል እውን ለማድረግ እውቀትና የአሰራር ስርዓት በአግባቡ ተዘርግቶለት ሊሰራ እንደሚገባው የቦርድ ሰብሳቢው አክለዋል።

አሰራሩ ከዚህ ቀደም ከነበረው የካርጎ አገልግሎት በእጅጉ የሚለይ እንደሆነ በማንሳት፤ ዕቃ ከውጭ ተጭኖ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ይወስድ የነበረውን እስከ 7 ቀን በአዲሱ አሰራር እንደሚቀረፍ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎና ሎጀስቲክስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቤል አለሙ፣ አየር መንገዱ በ15 ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እያስገነባ ያለው የኢ-ኮሜርስ ማዕከል በመጪው የፈረንጆቹ 2023 አጋማሽ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በዓለም ካሉ ትልልቅ የኢ-ኮሜርስ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር እየሰራ ሲሆን በሀገር ውስጥ ዘርፉን ለመደገፍም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በዓለም ላይ በፍጥነት እየተሰራበት ያለውን ፈጣን የካርጎ አሰራር በመከተል የሚሰራ ሲሆን በሀገር ውስጥ ገቢና ወጪ ዕቃዎች በዚሁ አሰራር እንዲታገዙ ይደረጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የህግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ሙልጌታ በየነ በበኩላቸው፣ የዲጂታል ግብይት ስርዓቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለመውሰድ፤ ኮሚሽኑ ራሱን ለአሰራሩ እያዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ 2021 ካገኘው የ5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ውስጥ ከፊሉ ከጭነት አገልግሎት የተገኘ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም