በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የመሠረታዊ ፍጆታ ምርቶች ከውጭ እየገቡ ነው-የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር

33

ባህር ዳር፣ ጥቅምት 21/2015(ኢዜአ) በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ የተከሰተውን እጥረት ለማቃለል በ100 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ዘይት እና ስኳር ከውጭ ሀገራት እያስገባ መሆኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ያለፉት 3 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙን የሚገመግም መድረክ በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ይገኛል።

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረመስቀል ጫላ በመድረኩ እንደተናገሩት እየተስተዋለ ያለውን የዋጋ ግሽበት ለማቃለል መንግስት እየሰራ ነው።

በመሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ያለውን ክፍተት ለማጥበብም 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መድቦ ዘይትና ስኳር ከውጭ ሀገር እያስገባ መሆኑን አስታውቀዋል።

የተዘረጋው የነዳጅ ሪፎርምም የትራንስፖርት አገልግሎት ለሚሰጡ ተሽከርካሪዎች የታለመ የነዳጅ ድጎማ በማድረግ ግብይቱ በውጤታማነት እንዲመራ ማድረጉንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ዘመናዊ የንግድ አሰራር ስርዓት ለመዘርጋት በቴክኖሎጂ ታግዞ በተካሄደ ቀጥታ የምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትም በሩብ ዓመቱ ብቻ 202 ሺህ ነጋዴዎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።

"የሲሚንቶ ምርት ግብይትን ለማስተካከልና ስርጭቱንም ቅደም ተከተል ለማስያዝ በተደረገው ጥረት የሲሚንቶ የፋብሪካ መሸጫ ዋጋን ከመወሰን ባለፈ የመንግስት ፕሮጀክቶች እና ትላልቅ የግል የግንባታ ፕሮጀክቶች ቀጥታ ከፋብሪካዎች ሲሚንቶ እንዲወስዱ ተደርጓል" ብለዋል።

በአምራቹና ሸማቹ መካከል አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያስከትሉ ደላላዎችን ከእህል፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ እና ከቁም እንስሳት ንግድ ስርዓት እንዲወጡ መደረጉንም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈንታው ፈጠነ በክልሉ በሩብ ዓመቱ ውጤት ከተገኘባቸው ተግባራት መካከልም የነዳጅ ድጎማ ሪፎርም፣ የቀጥታ ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት እንዲሁም አዲስ የተዘረጋው የሲሚንቶ ሽያጭ መመሪያ እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል።

በክልሉ በሩብ ዓመቱ 169 ሺህ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

"የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት መቆጣጠር፣ እንዲሁም የውጭ ምርቶችን ማሳደግና በዘርፉ የሚስተዋሉ ህገ-ወጥ ንግድን የመቆጣጠር ሥራዎች ገና ያልተሻገርናቸው ችግሮች በመሆናቸው በቀጣይ ትኩረት ሰጥተን የምንሰራቸው ተግባራት ናቸው" ብለዋል አቶ ፈንታው።

ከምርት አቅርቦት ጋር የሚስተዋሉ እጥረቶችን ለማቃለል፣ ችግር ፈጣሪዎችን ከትስስሩ ለማውጣትና  የግብርና ምርቶችን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ይግለጠው አብዛ ናቸው።

በመድረኩም የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ንግድ ቢሮዎችና የጽህፈት ቤት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ሲሆን በቀጣይ ስራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫም ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም